ሕንድ ውስጥ ያሉ ወላጆች ከሴት ልጅ ይልቅ ወንድ ልጅ እንዲኖራቸው ባላቸው ፍላጎት የተነሳ 21 ሚሊዮን የሚደርሱ ‘ያለተፈለጉ’ ሴት ልጆች በሃገሪቱ እንዳሉ አንድ የመንግሥት ሪፖርት አመለከተ።
የሕንድ የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው በርካታ ጥንዶች ወንድ ልጅ ለማግኘት ሲሉ መውለዳቸውን ይቀጥላሉ።
ሪፖርቱን ያዘጋጁት ባለሙያዎች እንዳሉት ይህ ሁኔታ በፆታ ምርጫ ምክንያት ከሚደረገው የፅንስ ማቋረጥ የተሻለው አማራጭ ቢሆንም ለሴት ልጆች ሊሰጥ የሚገባው ትኩረትን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንሰው እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
በወላጆች መካከል ያለው የወንድ ልጅ ምርጫን በተመለከተ ”የህንድ ዜጎች ሊነጋገሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው” ይላሉ ባለሙያዎቹ።
የሪፖርቱ አዘጋጆች እንደደረሱበት ወንድ ልጅ እንዲኖራቸው የሚሹ ወላጆች ሴት ልጅ መፀነሷን ሲያውቁ በሚያደርጉት የፅንስ መቋረጥ ሳቢያ ከአጠቃላዩ የሃገሪቱ ህዝብ 63 ሚሊዮን ሴቶች እንዲጎድሉ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም የበለጠ እንክብካቤ ከሴት ልጅ ይልቅ ለወንድ ልጆች ይሰጣል።
ምንም እንኳን የፅንስን ፆታ ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ሕንድ ውስጥ ሕገ-ወጥ ቢሆንም ምርመራው ስለሚከናወን በፆታ ምርጫ ሰበብ ለሚካሄድ የፅንስ ማቋረጥ እድልን ፈጥሯል።
ወላጆች ወንድ ልጆችን እንዲመርጡ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ንብረት ለሴት ልጆች ሳይሆን ለወንዶች ስለሚተላለፍ፣ ጋብቻ ሲታሰብም የሴቷ ቤተሰብ ጥሎሽ እንዲሰጥ ስለሚጠየቅ እና ሴቶች ካገቡ በኋላ ወደባሎቻቸው ቤት ስሚገቡ እንደሆነ ይነገራል።
ይህን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ጠንካራ ወንድ ልጆች የማግኘት ምርጫን መሰረት አድርጎ አንድ የሃገሪቱ ጋዜጣ በሳይንስ ድጋፍ የሌለውን ወንድ ልጅ የማግኛ ዘዴዎች ብሎ እስከማተም አድርሶታል።
ጋዜጣው ካሰፈራቸው ዘዴዎች መካከል በመኝታ ጊዜ ወደ ምዕራብ ዞሮ መተኛት እና ከሳምንቱ ቀናት በተወሰኑት ውስጥ ግንኙነት መፈፀም ወንድ ልጅ ለማግኘት ይረዳል የሚል ይገኝበታል።
የወንድ ልጆች ምርጫ ከሚታይባቸው የሕንድ ግዛቶች መካከል ፑንጃብና ሃሪያና ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ግዛት ሜጋላያ ናት።
በፑንጃብና ሃሪያና ግዛቶች ከሰባት ዓመት በታች ላሉ 1200 ወንድ ልጆች አንፃር 1000 ሴት ልጆች ብቻ እንዳሉ በተደረገው ጥናት ተደርሶበታል።
Source: BBC amharic
The post India: The hell of 21 million unwanted Girls appeared first on Bawza NewsPaper.