የአሸንዳ በዓል አከባበር ቅድመ ስርዓት የራሱ የሆነ ቅድመ ዝግጅት አለው። ይህም እንደየአካባቢው ሁኔታ ይለያያል። አንዳንድ አካባቢዎች ከአንድ ወር በፊት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ወደ ገጠሩ ደግም ከበዓሉ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅቶች ይጀምራሉ።
በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት የበዓሉ ዋና ተዋናይ ልጃገረዶች እንደመሆናቸው ለበዓሉ በመንፈስም ሆነ በቁሳቁስ ቀድመው ይዘጋጃሉ። ዝግጅቱም በቡድን አመሰራረትና የስራ ድርሻ ክፍፍል ጀምሮ እስከ አልባሳት፣ ጌጣጌጥና ከመዋቢያ ቁሳቁሶች ማሰባሰብ ሟሟላት ድረስ ይደርሳል። የቡድን አመሰራረቱም ሰፈርን ወይንም መንደርን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ በአንድ ቡድን ውስጥ እንደሁኔታው ከ5 እስከ 40 ልጃገረዶች ይሳተፋሉ።
በዚህ የቡድን ጨዋታ በቅድሚያ በባህሪዋ መልካም የሆነች፤ በማስተባበር ብቃቷ የተመሰከረላትና በእድሜዋ ከሁሉም ከፍ የምትለዋ ልጃገረድ በቡድን አባላቱ ተመርጣ ቡድኑን ትመራለች። ይህች ልጃገረድ እንደ የአካባቢው ሁኔታ የቡድኑ መሪ፤ /ሃለቃ/ በመባል ትጠራለች።
የቡድኑ መሪ/ሃለቃ/አመራርጥ የመምራት ብቃትና ችሎታ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ዘፈን ማውጣት፣የማጫወት ዕውቀትና ታማኝነትንም መሰረት ያደርጋል።
ይሁንና ልጅቱ የሚጠበቅባትን ሃላፊነት መወጣት ካልቻለች የቡድኑ አባላት በምትኳ ሌላ የመምረጥ ስልጣን አላቸው። በመቀጠል በቡድኑ ውስጥ ገንዘብ ያዢ፣ ጥሩ ከበሮ የመምታት ብቃት ያላቸው ልጆች እንዲሁም በድምፃቸው ጥሩ የሆኑ ሁለት ልጃገረዶች ይመረጣሉ። ከሁለቱ በግጥም ችሎታዋና በድምፅ አወጣጥዋ ጥሩ የሆነችው ዋና የዘፈኑ መሪ ትሆናለች። ልጃገረዶቹን የሚያጅቡ ሁለት ወንዶች ቡድኑን ይቀላቀላሉ።
ይህ ከሆነ በኋላ የአልባሳት ጌጣጌጥና ሌሎች መዋቢያ ቁሳቁሶች ስለመሟላቱ ይወያያሉ። ሁሉም ልጃገረዶች ከወላጆቻቸው አዳዲስ አልባሳትና ጌጣጌጥ አስገዝተው አሊያም ከዘመዶቻቸው ተውሰው ለበዓሉ ይዘጋጃሉ።
ለበዓሉ የሚሆን ዘፈን ይመርጣሉ፤ ጨዋታውን እንዴት መጫወት እንዳባለባቸው ይመክራሉ። ወላጆች በበኩላቸው ባህሉን ከማስቀጠል አኳያ ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ሁሉ ለማሟላት ይጥራሉ። በአብዛኛው አልባሳት በመግዛት ቢቸገሩ እንኳ ይለብሱት የነበረውን ልብስ በማጠብ፣ ፀጉራቸውን ሹሩባ በማሰራት፣ ከበሮ በማዘጋጀት፣ የአሸንዳ ቅጠል ከበረሃ በማምጣት አሊያም በመግዛት ልጆቻቸው ለአሸንዳ በዓል ጨዋታ እንዲዘጋጁ ያደርጋሉ።
የዋዜማው እለት ነሐሴ 15 ቀን ኩል ይኳላሉ፣ ቅቤ ይቀባሉ ፣ ሹሩባ ይሰራሉ። የጆሮና የአንገት ጌጣጌጦችን ማድረግ ፣ ጥሩ ቀሚስ እና ጫማ ያደርጋሉ። ወላጆቻቸው የአሸንዳ ቅጠሉን በነጭ ዘርፍ በኩል ወደታች በማድረግ በገመድ እያሰሩ ልጆቻቸውን ለበዓሉ ያዘጋጃሉ። በመጨረሻም በበዓሉ ዕለት የሚሰባሰቡበትን ሰዓት ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ።
የአሸንዳ ልጃገረዶች በተለየ መልኩ “ጓል አሸንዳ” በመባልም ይጠራሉ። በዚህ መልኩ ቅድመ ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የበዓሉ ዋዜማ ሌሊት ከቤታቸው በመጠራራት ለመሰባሰቢያ የሚገለገሉበትን “ወንዙን ተሻግራ አሸንዳ መጣች፤” እያሉ በመዝፈን ወደ ወንዝ /ምንጭ/ ይሄዱና እግራቸውን፣ እጃቸውን፣ ፊታቸውን ይታጠባሉ።
ይህ የመታጠብ ስርዓትም ተምሳሌትነት አለው። በአካልም ሆነ በመንፈስ መፅዳትን ንፁህ የመሆን ምልክትን ይወክላል። ስርዓተ ጊዜው ነሐሴ 16 የመጀመሪያው ቀን ነው። በዚህ ዕለት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠሉን እርስ በእርሳቸው በወገባቸው ዙሪያ ይተሳሰራሉ። ከጥጥ የተሰራ መቀነት ለሁለት ግራና ቀኝ በመዘርጋት በሁለት ትከሻቸው ዙሪያ አንዷ ለአንዷ በማጣፋት ይለብሳሉ። አለባበሳቸውም በትከሻቸውና በብብታቸው ስር ተጣፍቶ ጥለቱን በሁለቱም ትከሻዎቻቸው ፊት ለፊት እንዲመጣ በማድረግ ነው። ሲቀጥልም ከቅል ውስጥ ቅቤ እያወጡ እርስ በእርስ በሹሩባቸው ላይ ይቀባሉ። ሁሉንም ዝግጅታቸውን አስተካክለው፣ አምረውና ተውበው ለጨዋታው ዝግጁ ይሆናሉ።
በዚህ መልክ ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከተለያየ አቅጣጫ ግንባራቸውን በእጃቸው ያዝ ቀና እያደረጉ ለጨዋታው እንዲሰባሰቡ ከጓደኞቻቸውጋር የመግባቢያ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት በሚደረግ የአጠራር ዘይቤ መሰረት በድምፅ ይጠራራሉ። ከበሯቸውን እየመቱ እየዘፈኑ ወደ ጋራ የመሰባሰቢያ ቦታቸው በመውጣት ከተገናኙ በኋላ በጋራ ክብ ሰርተው ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።
ቀልብ በሚገዛ ዜማ የሚያንቆረቁሩት ግጥም ሲተረጎም፤ “መጣች መጣች አሸንዳ፣ መጣች የአምናዋ አሸንዳ፣ ዛሬ ተገናኘን፣ ክብ ሰርተን እንደሸንበቆ ተደርድረን አሸንዳ እያልን እንደማይቀረው ልምድና ወግ እንደአምናው እንጫወት” ማለት ሲሆን፤ ጭፈራውም በዚሁ ግጥምና ዜማ ይደምቃል። በጨዋታው ልጃገረዶቹን ሁለት ወጣት ወንዶች ባለ አራት ቁንጮና ባለግማሽ ፀጉር አብረዋቸው ዳር ዳሩን ይጫወታሉ።
ወንዶች በአለባበሳቸው ቅጠልያና ሰማያዊ ቴትሮን ቁምጣና እጅ ጉርድ ኮት በአዝራር የተዋበና ያሸበረቀ፣ በትከሻቸው ቦርሳ ያነግታሉ። መፋቂያ በአፋቸው ይይዛሉ። ዱላቸውን ወደ ላይ በማወዛወዝ ክብ ሰርተው የሚጫወቱትን ልጃገረዶች እየጨፈሩ ይዞሯቸዋል፤ ይጠብቋቸዋል።
ልጃገረዶቹ ጨዋታውን እያደመቁ ከቀጠሉ በኋላ የመጀመሪያ ተግባራቸው አንድ ላይ በመሰባሰብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን መሄድ ነው። ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱም የሚዘፍኑት ዘፈን ያላቸው ሲሆን፤ ዘፈኑም እንደቤተክርስቲያኑ ደብር ስያሜ የሚወሰን ነው። ቀጥለውም አንድ ላይ ሁሉም ተጫዋቾች በመሰባሰብና እልል በማለት የቤት ለቤት ጨዋታቸውን ይጀምራሉ። በየደረጃው ሁሉንም ያደርሳሉ። ጨዋታው እንዲሞቅላቸው ክብ እየሰሩ፣ እየዞሩ፣ ወደፊትና ወደኋላ መጣ ሄደት እያሉ ከእግራቸው ዘለል ዘለል እያሉም እጅግ በሚያስደስት የጨዋታ ምት በደስታ እየተዝናኑ ያዝናናሉ።
በዚህ ሁኔታ ጨዋታው እየደመቀ ሲሄድ፤ ህፃን ልጅ ትከሻቸው ላይ በማቆም «አንቺ አይነ ቆንጆ ውብ ልጃገረድ እንዳትወድቂ» በማለት እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ህጻኗም ትከሻ ላይ ሆና መስታወት እንደማየት፤ ኩል እንደመኳል በሚመስል ውዝዋዜ ትከሻዋ ላይ እጇን እያደረገች ጭፈራ ታሳያለች። በዓሉም በሞቀ መልኩ በተለያየ ትዕይንት ቀጥሎ በመጨረሻ ጨፋሪዎቹ የዛሬ ዓመት ያገናኘን እየተባባሉ ወደየመጡበት ይሄዳሉ።
ምንጭ:- አዲስ ዘመን ጋዜጣ
The post አሸንዳ appeared first on Bawza NewsPaper.