አሁን ላይ አንድ ሰው እድሜው 100 ዓመት ውስጥ ከገባ ከፍተኛ እድሜን ያስቆጠረ ተደርጎ ይወሰዳል።
ተመራማሪዎች ግን በሁለት የትውልድ ዘመን ውስጥ የሰው ልጅ አማካይ የመኖሪያ እድሜ እስክ 125 ዓመት ሊደርስ ይችላል ብለዋል።
እስካሁን በዓለማችን ላይ በርዝመቱ በክብረ ወሰን የያዘው እድሜ የ122 ዓመት ሲሆን፥ ክብረ ወሰኑም የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት የፈራንሳዊቷ ጄን ካልሜንት ናቸው የያዙት።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ1997 በ122 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የጄነን ያክል በምድር ላይ የኖረ ሰው የለም ተብሏል።
የኔዘርላንድስ ተመራማሪዎች ግን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2070 የአንድ ሰው አመካኝ የመኖሪያ እድሜ ጣራ 125 ሊሆን እንደሚችል ተንብየዋል።
ይህንን ቀድመው የሚያሳኩት ደግሞ የጃፓን ሴቶች ናቸው ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የመኖሪያ እድሜ ያላቸው ጃፓናውያን በመሆናቸው ነው።
ከኔዘርላንድስ ግሪኒገን ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ተመራማሪዎች፥ በፈረንጆቹ 2070 የሰው ልጅ የመኖሪያ እድሜ ጣራ ይጨምራል ያልነው በአሁኑ ጊዜ እድሜያቸው ከ100 ዓመት ያለፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ነው ብለዋል።
በእንግሊዝ ብቻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2015 የተመዘገበው እድሜያቸው ከ100 ዓመት ያለፉ ሰዎች ቁጥር 14 ሺህ 500 ሲሆን፥ ይህም በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን እንደሚደርስ ይጠበቃል።
ሆኖም ግን በ2070 የሰዎች አማካይ የእድሜ ጣራ 125 ይደርሳል የተባለው ጥናት፥ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ተመራማሪዎች የተሰራው እና አማካኝ ሰዎች የእድሜ ጣራ 115 ይሆናል የሚለው ጥያቄ አስነስቶበታል።
የአሜሪካ አጥኚዎች እንደሚናገሩት እንደ አውሮፓውያኑ በ2070 የ125 ዓመት እድሜ ያለው ሰው ከ20 ሺህ ሰዎች አንዱ ብቻ ለሆን ይችላልም ብለዋል።
የግሪኒገን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ፋንይ ጃንሰን፥ “እድሜያቸው ከ100 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፤ ይህም የሰው ልጅ የመኖሪያ እድሜ እየጨመረ ለመሄዱ ማሳያ ነው” ብለዋል።
“ሰዎች ከዚህ በፊት ከነበረው በላይ የሚኖሩበት የእድሜ መጠን እየጨመረ ነው፤ ይህም የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል ፕሮፌሰር ፋንይ።
ለዚህ ምክንያቱ የሰዎች የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መሻሻል፣ የተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤ፣ የመኖሪያ ቤት ሁኔታ መሻሻል እና ለሰው ልጅ የሚሰጠው ህክምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ መምጣታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
The post በ2070 የሰው ልጅ አማካይ የመኖሪያ እድሜ 125 ዓመት ይሆናል appeared first on Bawza NewsPaper.