Quantcast
Channel: Bawza
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ለምን?

$
0
0

በኢትዮጵያ የተለያዩ የካንሰር ሕመሞች በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  መታየት ጀምረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ችግር ያልነበሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ጫና ፈጥረዋል፡፡

በተለይ ከአመጋገብ፣ ከአኗኗር ዘይቤና ከባህሪ ጋር በተያያዘ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በካንሰር የመጠቃት እድላቸው እየሰፋ መጥቷል፡፡ በተላላፊ በሽታዎች ለምሳሌ ኤችአይቪ ከሚፈጠረው በሽታን የመቋቋም አቅም መዳከም ጋር ተያይዞም ‹‹ሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ›› የሚያስከትለው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ነው፡፡ አንዳንዴም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የሚፈጥሩት የጤና መቃወስና የአቅም መዳከም ለካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡

ለካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እየጨመሩ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም ያለው አቅም አናሳ ነው፡፡ በነዚህም ምክንያቶች በኢትዮጵያ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በሽታን ቀድሞ በመከላከል ላይ መሠረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ለዚህ ምን ምላሽ አለው?

በኢትዮጵያ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ ሕክምና የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ በተለይ በክልሎች ላይ ሕክምናው የሚሰጥበት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የካንሰር ሕሙማን አዲስ አበባ መጥተው ለመታከም ግድ ይላቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በአዲስ አበባ የካንሰር ሕሙማንን ለማስተናገድ የሚችል በቂ አቅም የለም፡፡ ለከተማዋም ሆነ ለአገሪቱ ብቸኛ የሆነው የጨረር ሕክምና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ሲገኝ፣ እሱም ሕሙማንን ለመድረስ አልቻለም፡፡

በአገሪቱ በዓመት እስከ 60 ሺሕ የሚደርሱ አዳዲስ ሕሙማን የሚመዘገቡ ሲሆን፣ ቀዶ ሕክምናን፣ ጨረርንና ኬሞቴራፒን በጥምረት የሚሰጠው ጥቁር አንበሳ፣ ከአቅሙ በላይ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎቹ የጨረር ታካሚዎች ግልጋሎት ለማግኘት እስከ ስድስት ወራት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ መሃል የሚሞቱት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑም በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡

የኬሞቴራፒ ሕክምናውም ቢሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ጥቂት ተሽሎ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተጨማሪ በግልና በመንግሥት ተቋማት ቢጀመርም፣ ተደራሽ አይደለም፡፡ ለአገሪቱም ሆነ ለመዲናዪቱ አዲስ አበባ የጤና ዘርፍ ጫና እየሆነ የመጣውን የካንሰር ሕመም ቀድሞ ለመከላከል፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ቢጀመርም የተረዳሽነትና የግንዛቤ ችግር አለ፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ሒደት ድጋፍና ክትትል ኦፊሰር አቶ ኢዮቤድ ካሌብ እንደሚሉት፣ ካንሰርን ቀድሞ መከላከል የሚቻልበትን አገልግሎት በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች  ላይ ለመፍጠር ተሠርቷል፡፡ በዋነኛነት ካሉት የካንሰር ሕመሞች የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ቀድሞ ከታወቀና ከተደረሰበት የመዳን ዕድል አለው ተብሎ ስለሚታሰብ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የድርጊት መርሐ ግብር እ.ኤ.አ. በ2015 የወጣ ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ እንደሰፈረውም፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ1996 እስከ 2008 ሕክምና ከተደረገላቸው የካንሰር ሕሙማን 30.3 በመቶው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ሕሙማን ነበሩ፡፡

መንግሥት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ላይ የተወሰነውን የካንሰር ሕክምና በክልሎች በሚገኙ አምስት ሥፍራዎች ለማስፋፋት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎንም በየዓመቱ እስከ አራት ሺሕ የሚደርሱ ሴቶችን የሚቀጥፈውን የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም እየሠራ ይገኛል፡፡

እንደ አቶ ኢዮቤድ፣ በ22 ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች እንዲሁም በግል ክሊኒኮች የማሕፀን ጫፍ ቅድመ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ የካቲት 12፣ ጋንዲ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ አለርት ሆስፒታሎች እንዲሁም ሜሪስቶፕስና ሜሪጆይ ክሊኒኮች የቅድመ ምርመራ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ምልክት ከታየና በተቋማቱ ደረጃ ሊታከም የሚችል ከሆነ፣ እዚያው የሚታከም ሲሆን፣ ከተቋማቱ አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ የሕክምና አገልግሎቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ይሰጣል፡፡ በቅርቡ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ይጀመራል፡፡

የኬሞቴራፒና ሬዲዮቴራፒ አገልግሎት ፈላጊዎች የመብዛታቸውን ያህል አገልግሎቱ ባይሰፋም፣ በኬሞቴራፒ አገልግሎት በኩል ያለውን ችግር ለማቃለል ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመሆን የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ጤና ጣቢያ ሙሉ ለሙሉ የኬሞቴራፒ ሕክምና መስጫ ተደርጓል፡፡ ለጊዜውም 30 ያህል አልጋዎች አሉት፡፡

ለማሕፀን ጫፍ ካንሰር ተጋላጭ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

ለግብረሥጋ ግንኙነት የደረሱ ሴቶች ለማሕፀን ጫፍ ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በተለይ ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ተጋላጭ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ግብረሥጋ ግንኙነት ቀድመው የጀመሩት ካልጀመሩት ሲነፃፀሩ ለካንሰሩ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ዘላለም መንግሥቱ እንደገለጹት፣ ከ20 ዓመት በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መጀመር ለበሽታው ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡ ከአንድ በላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አጋር መኖርና ለአባለዘር በሽታዎችም መጋለጥ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሰውነት በሽታ የመቋቋም አቅሙ ሲቀንስ ለምሳሌ በደም ውስጥ ኤችአይቪ መኖርም የሚያጋልጥ ሲሆን፣ ሲጋራ ማጨስና የሚጨስበት ቦታ በብዛት መገኘት ምክንያቶቹ ናቸው፡፡ በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ ለሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ ደግሞ ለማሕፀን ጫፍ ካንሰር ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡

ሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ ምንድን ነው?

ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ በቆዳ ንክኪ ከሰው ወደሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው፡፡ ከ100 በላይ ዓይነቶች ሲኖሩት፣ 40 ዓይነቶቹ አደገኛና የመራቢያ አካላትን፣ አፍን ወይም ጉሮሮን የሚጎዱ ናቸው፡፡ መተላለፊያቸውም ግብረሥጋ ግንኙነት ነው፡፡ ሴንተር ፎር ዲሲዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሪቬንሽን (ሲዲሲ)፣ ሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ በግብረሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍና ወንዶችንም ሴቶችንም የሚጎዳ ኢንፌክሽን እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ቫይረሱ ምልክት ሳያሳይ የሚቆይ በመሆኑም ሳይታወቅ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድልም አለው፡፡ ከማሕፀን ጫፍ ካንሰር በተጨማሪም ለመራቢያ አካላትና ለጭንቅላት፣ ለአንገትና ለጉሮሮ ካንሰር ይዳርጋል፡፡

ሂዩማን ፓፒሎማቫይረስ በሽታን የመከላከል አቅም ሲዳከም ከሚከሰቱ የቫይረስ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን፣ በልቅ ግብረሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ መሆኑን አቶ ዘላለም ይገልጻሉ፡፡ ለማሕፀን ጫፍ ካንሰር ዋነኛ መንስዔ ሲሆን፣ ሰውነትን የመጉዳት ሒደቱ አዝጋሚ ነው፡፡ የማሕፀን ጫፍ ካንሰርም ስር እስኪሰድ ከ15 እስከ 20 ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፡፡

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እስከምን?

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ቀድሞ ከታወቀ በቀላሉ ይታከማል፡፡ ሆኖም በታዳጊ አገር ለሚገኙ ሴቶች ዋነኛ የሞት ምክንያት ነው፡፡ በዓለም ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በማሕፀን ጫፍ ካንሰር የሚያዙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ያህሉ ይሞታሉ፡፡

እንደ አቶ ዘላለም፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በዓመት 7,095 ሴቶች ለማሕፀን ጫፍ ካንሰር ይጋለጣሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 4,732 ያህሉ ይሞታሉ፡፡

በአገሪቱ በስፋት እየተስተዋለ የመጣውን የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ቀድሞ ለመከላከልና ችግሩ ስር ሳይሰድ ለማከም በከተማ ደረጃ ለአቅመ ሔዋን ከደረሱት ውስጥ ማለትም፣ ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል 10 በመቶ ያህሉን በቅድመ ምርመራ ለማሳተፍ ቢታሰብም፣ አቶ ኢዮቤድ እንደሚሉት፣ መድረስ የተቻለው አራት በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡ የተመርማሪው ቁጥር ያነሰው የግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ካለው ክፍተትና አገልግሎት የሚገኝበትን ሥፍራ በስፋት ካለማስተዋወቅ ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ ለበሽታው ተጋልጠው የተገኙ ቢኖሩም የታሰበውን ያህል ብዙዎች ስላልተመረመሩ ቁጥሩን ለመናገር ያግዳታል፡፡ ሆኖም ችግሩ በስፋት እንዳለ ይታመናል፡፡

ከማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ፓፒስሚርና ቪአይኤ የተባሉ ቅድመ ምርመራ ዘዴዎች አሉ፡፡ ፓፒስሚር ከማሕፀን ጫፍ ናሙና በመውሰድ የሚደረግ ምርመራ ሲሆን፣ በአብዛኛው በደሃና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች አይገኝም፡፡

ቪአይኤ የተባለውና ማሕፀን በር ላይ መመርመሪያ በመቀባት በእይታ ውጤቱን ማወቅ የሚቻልበት ዘዴ ግን በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ቪአይኤ ምንም ዓይነት ሕመም የማይፈጥር የምርመራ ዘዴ ሲሆን፣ ምርመራውም ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ብቻ ይወስዳል፡፡ የቅድመ ካንሰር ምልክት ከታየ ወዲያውኑ እዚያው ሕክምናው ይሰጣል፡፡ ስር ከሰደደ ከፍተኛ ሕክምና ማግኘት ግድ ነው፡፡

በቅድመ ካንሰር ምርመራ ጊዜ አንዲት ሴት ምልክቱ ካልታየባትና ኤችአይቪ በደሟ ከሌለ በየአምስት ዓመቱ ክትትል እንድታደርግ የሚመከር ሲሆን፣ ኤችአይቪ ካለባት ደግሞ በየሦስት ዓመት መታየት ይኖርባታል፡፡

እንደ አቶ ኢዮቤድ፣ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ ቀላልና ችግሩ ቶሎ ከተደረሰበትም ታክሞ የመዳን ዕድል አለው፡፡ ሆኖም ብዙዎች ለምርመራ እየመጡ አይደለም፡፡ በሽታው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በመሆኑም በተለይ ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ እንዲከላከሉና ቀድመው እንዲያውቁ ይመክራሉ፡፡

The post የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ለምን? appeared first on Bawza NewsPaper.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Trending Articles