በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በተመራ የጥናትና ምርምር ቡድን ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ፓርኩ ከደረሰበት የእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ ለማገገምና ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ከ10 ዓመታት በላይ ሊወስድበት እንደሚችል በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡ ተገለጸ፡፡
በተከሰተው የእሳት አደጋ በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ ወካይ እንስሳት ማትም በዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮ ላይ ምንም ዓይነት የሞት አደጋ አለመከሰቱን በቅኝት መረጋገጡም ነው የተገለጸው፡፡ የቀይ ቀበሮ ምግብ የሆነው ትልቁ ፍልፈል እና የዱር አይጦች ተቃጥለው መገኘታቸውን የጠቆመው ጥናቱ አሁንም በቂ ሊባል የሚችል ቁጥር ያለው የፍልፈልና የአይጥ ዝርያ በፓርኩ ውስጥ መኖሩን አረጋግጧል፡፡
በበርካታ የአእዋፍ ዝርያ ስብጥሩ የሚታወቀው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ 180 ገደማ የአእዋፍ ዝርያዎች መዳረሻ ነው፤ ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ በፓርኩ ወሳኝ ቀጠና በተለይም በአስታ የዛፍ ዝርያ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ምክንያት ያጋጠመ የአእዋፍ ሞት አለመከሰቱ በዳሰሳው ተመልክቷል፡፡ አደጋው የተከሰተበት ወቅትም ለአእዋፍ የመራቢያ ወቅት የነበረ ባለመሆኑ ምክንያት መኖሪያቸው ከመውደሙ ባሻገር በአእዋፍ ላይ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ተጠቁሟል፡፡
በአጠቃላይ በመጋቢት ወር ውስጥ በፓርኩ የተለያዩ ቦታዎች መነሻው ባልታወቀ ምክንያት ሁለት ጊዜ ተከስቶ ለሳምንታት በዘለቀው የእሳት አደጋ የፓርኩ 2 ነጥብ 5 በመቶ ማለትም 1040 ሄክታር መውደሙ ይታወቃል፡፡ በዚህም 476 ነጥብ 12 ሄክታር በአስታ ዛፍ የተሸፈነ መሬት እና 563 ነጥብ 88 ሄክታር በሳር የተሸፈነ መሬት ተቃጥሏል፡፡
በአጠቃላይ በፓርኩ ላይ በደረሰው የሰደድ እሳት አደጋ ምክንያት በፓርኩ ሥነ ምኅዳር እና በሀገር ገጽታ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን ያመለከተው ጥናቱ በአንጻሩም ኅብረተሰቡ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ በተወሰነ መልኩ መለወጡ እና የመረጃ አውታሮች ትኩረት እንዲሆን ማስቻሉን አመላክቷል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ ፓርኩ እንዲያገግም በተለያዩ አካላት በተዋረድ ምን ምን ሥራዎች መሠራት እንደሚገባቸውም አሳይቷል፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቸኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ብሔራዊ ፓርክ ነው፤ አጠቃላይ ስፋቱም 412 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የተቃጠለው የፓርኩ ክፍል በቅርቡ ከአደጋ ዝርዝር የወጣውን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ወደ አደጋ መዝገብ ሊያስገባው እንደማይችል ከዚህ በፊት መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
(አብመድ)