አዲስ አበባ በሚቀጥለው ሳምንት ዲጂታል የነዋሪዎች መታወቂያ መስጠት ትጀምራለች፡፡
አዲስ አበባ ዲጂታል የነዋሪዎች መታወቂያ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ መስጠት እንደምትጀምር የከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኤጀንሲው የነዋሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራሂም እንዳሉት÷ ተቋሙ አገልግሎቱን ለማዘመን እየሰራ ነው።
አዲሱ የዲጂታል መታወቂያ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አገልግሎቱ የሚጀመር ሲሆን÷ ለዚህም በቂ መታወቂያ ካርዶች መዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአዲሱ መታወቂያ አሰጣጥ ጥንካሬና ድክመት ታይቶ በቀጣይ በሁሉም ክፍለ ከተማ ወረዳዎች መስጠት ይጀመራል ብለዋል።
አዲሱ መታወቂያ የብሔር ማንነትና የትውልድ ቦታ የሚገልጽ ይዘት የሌለው ሲሆን÷ በአንጻሩ የደም ዓይነት እንዲጠቀስ መደረጉም ተገልጿል።
የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺና የሞት ወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች ከሐምሌ 30ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ማዕከል የሶፍትዌር ምዝገባ በዘመናዊ መልኩ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የአጄንሲው የመረጃ ቅበላና ማስረጃ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ካሳ ተናግረዋል።
ሆኖም የነዋሪዎች አገልግሎት በተበታተነ መልኩና በወረቅት ላይ የተመሰረተ እንደነበር ያነሱት አቶ አንተነህ፤ አሁን አገልገሎቱን ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የነዋሪዎች የመታወቂያ አገልግሎትን ማዘመን ከከተማ አስተዳደሩ ቁልፍ ስራዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድ ለዚሁ ሥራ በጀት ተመድቦለት ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የነዋሪዎች መታወቂያ አገልግሎት መዘመን በመታወቂያ ማጭበርበርን ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መታወቂያ አሰጣጡ ደረጃውን የጠበቀና በአሻራ የተደገፈ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ደህንነቱ የተጠናከረ የነዋሪዎች መረጃ ምዝገባ ሶፍትዌር፣ የመታወቂያ ማተሚያና የአሻራ መቀበያ መሳሪያዎች መዘጋታቸውንም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የኢንተርኔት አቅርቦትን የሚፈለግ በመሆኑ የኔትወርክ መቆራረጥ እንዳያጋጥም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰሩ ነውም ብለዋል።
ነባሩ መታወቂያ በዲጂታል ሙሉ ለሙሉ እስኪቀየር ድረስ የወረቀት መታወቂያ አሰጣጡ እንድማይቋረጥም አቶ መሐመድ ገልጸዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 ነዋሪ አቶ ልዑልሰገድ በላይ እስካሁን ያለው መታወቂያ አሰጣጥ ዘመናዊ አይደለም፤መታወቂያውም ኤሌክትሮኒክ አለመሆኑ በቀላሉ ለብልሽት ይዳረጋል ይላሉ።
ከተማ አስተዳደሩ አሁን ዲጂታል መታወቂያ ልጀምር ነው ማለቱ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት አቶ ልዑል ሰገድ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግም ማጭበርበርን መቀነስ ይግባል ብለዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ሊጀመር መሆኑ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የተናገሩት የዚሁ ወረዳ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ውዱ አሰፋ፤ አንድ ሰው የነዋሪነት መታወቂያ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲያወጣ በማድረግ የተለያየ መታወቂያ በማውጣት የሚሰሩትን ወንጀል ያስቀራል ብለዋል።
በተለይ የጣት አሻራ እና የአይን አሻራ የሚወስድ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም መሆኑ አገልግሎቱን ለማዘመን፣ ለህጋዊ ማስረጃዎች ተዓማኒነት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ነው ያነሱት።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የወሳኝ ኩነት ምዝግባና ነዋሪዎች አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መልዓከ ብርሃኑ፤የነዋሪዎችን አገልግሎት የማዘመን ሂደቱ የግብዓት እና የሰራተኛ እጥረትን ከመቅረፍ መጀመር አለበት ነው ያሉት።
የከተማው ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ በቅድሚያ ብቁ የሰው ሃይል፣ ግብዓትና ምቹ የቢሮ ሁኔታ ፈጥሮና አሟልቶ ወደ አገልግሎት እንዲገባም ጠይቀዋል።
የነዋሪዎች አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ ማዘመን ሰው ሰራሽ ስህተቶችን ለመቀነስ፣ ወንጀሎችን ለመከላከል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የወሳኝ ኩነት ምዝግባ የነዋሪዎች አገለግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መሐመድ አብዱራሂም፤ በየወረዳዎቹ የነዋሪዎች አገልግሎትን ለማዘመን ሰራተኞች በተለያየ ዙር እየሰለጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በማዕከል ደረጃ አዲስ ለሚጀምረው የነዋሪዎች አገልገሎት አሰጣጥ 20 ብቁ የአይሲቲ ባለሙያዎች ከመደበኛ ሰራተኞች በተጨማሪ መመደባቸውንም አንስተዋል።
ምንጭ፡- ኢ.ዜ.አ