Quantcast
Channel: Bawza
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Fast of Nineveh (ወይዘሮ ነነዌ እና ሽማግሌው ዮናስ)

$
0
0

በጥንት ዘመን በአንድ ትልቅ ሀገር ነነዌ የምትባል ወይዘሮ ትኖር ነበር፡፡ ቀድሞ እግዚአብሔርን በፍጹም ነፍሷ በፍጹምም ሀሳቧ ትወደውና ትፈራው ነበር፡፡ ቆይታ ግን እግዚአብሔርን መፍራት ይቅርና ከነመኖሩም ረሳችው፡፡ በዚህም የተነሣ ከኃጢአት ሁሉ ቆጥራ ሁሉንም ሠራቻቸው፡፡ ተይ የሚልም አልነበረም፤ ሁሉም እርሷን ይተባበሩ ነበር እንጂ፡፡ ነነዌ ባለትዳር ሆና ሳለ እንደጋለሞታ የሚያስቆጥራትን ሥራ ሠርታለችና የእርሷ ወይዘሮነት የስም ብቻ ሆነ፡፡

ይህን ክፉ አኗኗሯን ያየ ጌታም ወደእርሱ ያቀርባት ዘንድ ዮናስ የተባለ ሽማግሌን ላከባት፡፡ ሽማግሌው ዮናስ ግን ወደወይዘሮ ነነዌ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም ነበር፡፡ ሄደህ ለዚያች ለነነዌ ንገራት በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ ወደማንነትሽ ባትመለሺ በመኣት እመጣብሻለሁ ብሎሻል በላት ቢለው እምቢ ብሎ ከአምላኩ ፊት ኮበለለ፡፡

ተርሴስ ወደምትባል ቦታ በመርከብ ሲሄድ ያልጠበቀው ነገር ገጠመው፡፡ መርከቧ እስክትሰጥም ድረስ በማዕበል ተጨነቀች፡፡ በዚህም የተነሣ በውስጥ ያሉት ሁሉ ምን እናድርግ በማለት ተነጋገሩ፡፡ ዮናስንም ግብሩ ምን እንደሆነ ማንንም እንደሚያመልክ ጠየቁት፡፡ እርሱም አንዳች ነገር ሳይደብቅ ነገራቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የባሕር መናወጹ በእርሱ ምክንያት እንደመጣ አምኖ ወደጥልቁ ይጥሉት ዘንድ በራሱ ላይ ፈረደ፡፡ በራስ ላይ መፍረድን የመሰለ የለውጥ መጀመሪያ የት አለና!

ከመርከቡ ወደባሕሩ እንደተወረወረም ሞገዱ ጸጥ አለላቸው፡፡ እነርሱም ወደባሕር ስለጨመሩት ስለዚያ ሰው ኃጢአት እንዳያደርግባቸው እያዘኑ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ዮናስን ግን ዓሣ ነባሪው ዋጠውና ወደ አንድ ቦታ ወሰደው፡፡ ሽማግሌው ዮናስ በዓሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ ይጸልይ ነበር፡፡ ዓሣ ነባሪው ከወደብ ደርሶ ዮናስን ሲተፋው ስለደረሰባት ሀገር ጠየቀ፡፡ በሚገርም ሁኔታ አልሄድም ብሎ ወደተርሴስ የኮበለለባት የወይዘሮ ነነዌ ቦታ መሆኗን አወቀ፡፡ ከዚያም በፍጹም ቆራጥነት ነነዌን ያስተምር ዘንድ ወሰነ፡፡

ወደመንደሯ ገብቶም በሦስት ቀን ውስጥ ንስሐ ባትገባ እግዚአብሔር ምድሪቱን በእሳት እንደሚያጠፋት እግዚአብሔር የነገረውን አካፈላት፡፡ ነነዌም ልብ ብላ ሰማችው፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ አልነበረችም፤ የሚነገራትን ማስጠንቀቂያ ሁሉ በአንዱ ጆሮዋ ሰምታ በሌላኛው ታፈሰው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዮናስን ከመስማት አልፎ አዳመጠችው፡፡ የተነገራት መከራ ዛሬ የሆነ ያህል ሲሰማትም የመንደሯን ሰዎች ሁሉ ሰብስባ ጾም አወጀች፡፡ ጾሙም ለየት ያለ ነበር፡፡ እንኳን ሰው እንስሳት ሳይቀሩ ጥጆች ከላሞቻቸው ሳይገናኙ፣ ግልገሎች ከበጎች ወተት ሳይሹ ለሦስት ቀናት ጾሙ፡፡ እግዚአብሔርም የነነዌን ጾምና ጸሎት ተቀበለ፡፡ ሊያመጣባት ካሰበው መኣትና ቁጣም ተከለከለ፡፡

ነነዌ ማለት እኛ ነን፤ ዮናስ ደግሞ ደገኛ አባቶቻችን ናቸው፡፡ ተናጋሪ ብቻውን ዋጋ የለውም፤ ሰሚም የተናጋሪን ያህል ያስፈልጋል፡፡ መሰማትም በመናገር ብዛት አይደለም፤ እንዲሰሙ ሆኖ በመናገር እንጂ፡፡ ተናጋሪ ደገኛ አባት ቢኖርም እንደነነዌ በእዝነ ልቡና የሚያደምጥ ካልተገኘ ጉዳይ አይፈጽምም፡፡
“ተግሣጽም ለጠባይ ካልሆነው አራሚ፣
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ::” እንዲል ባለቅኔ፡፡
በነነዌ የሆነው ሁለቱም ነው፡፡ ዮናስ ተናገረ፤ ነነዌ ደግሞ አዳመጠች፡፡

እንዲህ እንደዮናስ ያለ ተናጋሪና እንደነነዌ ያለ አድማጭ ሲገኝ ሀገር ሁሉ ከጥፋት ይድናል፡፡ የነነዌን ንስሐ ለእኛም ያድለን፤ አሜን!

ጥር 20/2010 ዓ.ም

source: Menwagaw Temesgen Facebook page

The post Fast of Nineveh (ወይዘሮ ነነዌ እና ሽማግሌው ዮናስ) appeared first on Bawza NewsPaper.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Trending Articles