በወልዲያ ከተማ በጥምቀት በዓል ማግስት የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል።
መንግሥት የሟቾች ቁጥር ሰባት ነው ቢልም ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የሟቾችን እና የቁስለኞችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች እንደሰማነው ከሟቾቹ መካከል አዛውንቶች እና እድሚያቸው በአስራዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ሁለት ታዳጊዎች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በጥምቀት በዓል ማግስት ከተገደሉት መካከል በወልዲያ ከተማ በብረታ ብረት ሥራው የሚታወቀው ገብረመስቀል ጌታቸው ይገኝበታል።
ገብረመስቀል እድሜው ወደ 35 የሚጠጋ ሲሆን ባለትዳር እና የ5 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበር።
ገብረመስቀልን በቅርብ የሚያውቁት ጠንካራ ሰራተኛ ስለመሆኑ ይመስክሩለታል። ብረመስቀል የብረታ ብረት ድርጅት የነበረው ሲሆን በወልዲያ ከተማም የንግድ ህንጻ እየገነባ ነበር።
ገብረመስቀል በተገደለበት ቀን እና አሁን ቤተሰቡ ስለሚገኘበት ሁኔታ ወንድሙን ኪዳኔ ጌታቸውን አነጋግረነው ነበር።
ገብረመስቀል ጥር 12 የሚካኤል ታቦትን ሽኘቶ ሲመለስ መብራት ኃይል የሚባል ቦታ ላይ በጸጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች እንደተገደለ ከቤተሰቡ ሰምተናል። ወንድሙ ኪዳኔ ”ወንድሜን አምስት ቦታ ነው በሳስተው የገደሉት። እንዳይተርፍ ነው 5 ጊዜ በጥይት የመቱት” ሲል በምሬት ይናገራል።
ኪዳኔ ዕለቱን ሲያስታውስ ”ግርግር እንደተነሳ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩለት፤ አያነሳም። ብጠብቀውም መልሶ አይደውልም። በጣም ስለተጨነኩኝ ወደ ሆስፒታል ልፈልገው ሄድኩኝ።
”አንገቱ ላይ፣ ደረቱ ላይ፣ ሆዱ ላይ እና ብልቱ ላይ አምስት ጊዜ በጥይት የተመታ እና በደም የተሸፈነውን የወንድሜን አስከሬን ሆስፒታል ውስጥ አገኘሁ” ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ።
”ማመን ነው ያቀተኝ። ወንድሜ ላይ ግፍ ነው የተፈጸመው። ገብረመስቀል አንድ ጥይት የሚበቃው ልጅ ነበር። የቤተሰቡን አንጀት ነው የቆረጡት። እናቱን ወዳጅ፤ አባቱን አክባሪ ነበር። እሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን ነው የገደሉት። የአምስት ዓመት ሴት ልጅ አለችው አሁን የተፈጠረውን ነገር መቀበል አልቻለችም” ሲል ኪዳኔ በቁጭት ይናገራል።
The post ”ወንድሜን በአምስት ጥይት በሳስተው ነው የገደሉት” BBC appeared first on Bawza NewsPaper.