Quantcast
Channel: Bawza
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

ጎጃሜ ቡዳ ነው ተጠንቀቁት

$
0
0

ግዴላችሁም ይሄ ህዝብ ከሚዘፈንለትም በላይ ነው።ጎጃሜ ከሚገጠምለትም፣ከሚጻፍለትም የላቀ ምስኪን ነው።የምር የዋህ ነው፤ከወደደህ ከልቡ ነው [ከደረስክበትም ላይታገስህ ይችላል]። ከኣምስት ኣመታት በፊት ለጎጃም የነበረኝ ምስል ግን ኣሁን ከማወራው በተቃራኒ ነበር።
ኣንድ ድግሪ ለማግኘት ኣባይን እንድሻገር በትምህርት ሚኒስቴር ሲፈረድብኝ ስለጎጃሞች የማውቀው “ቡዳ” ናቸው የሚባለውን ብቻ ነው።የሚያውቁ ሰዎችም መከሩን-እኔና ጓደኞቼን።…”ኣንድ ጎጃሜ ለረጅም ጊዜ ወደ ኣንተ ካፈጠጠ ሊበላህ ስለሚሆን ‘ኣንተ ኣታፍጥብኝ’ ብለህ ቀልቡን ስትገፈው ይሸሽሃል፤ከቡዳው ንክሻም ትድናለህ” ኣሉን-ጎጃሜን ኣውቃለሁ የሚሉ የኛ ሰፈር ሰዎች ሁሉ!!
ይቺን በልቡ የከተበው ኣንዱ ጉዋደኛችንም ወደጎጃም የምንሄድበት ኣውቶቡስ ገና እንጦጦን ሳያልፍ መኪናው ውስጥ ”ወደኔ ኣፍጥጣ ተመልክታለች ያላትን ሴት ‘ኣንቺ ቡዳ ኣታፍጭብኝ ልትበይኝ ነው?!’ ኣላት” [ምክሩን መተግበሩ ነው በሱ ቤት]።እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው።
”ኡኡ እቴ ኣንተን በልቶ ማን ቃር ይሞታል።”’ ሃሃሃ… በጎጃሞች መደሰት የጀምርኩት በዚች ሴት ሳይሆን ኣይቀርም።
እኔ በስራም ሆነ በተለያየ ምክንያት በብዙ የሃገራችን ኣካባቢዎች ተዘዋውሬያለሁ።ነጭ ነጩን እንነጋገር ከተባለ ግን የጎጃም በተለይም የደብረማርቆስ ህዝብ ከሁሉም ይለያል።በራሱ ላይ ያለው እመነት የሚደንቅ ነው።በእኔ ዘመን የጉሊት ገበያውን ሲሸጥ ውሎ ሲመሽ በሸራ ጥቅልል ኣድርጎ ድንጋይ ጭኖበት ሄዶ በማግስቱ ሲመጣ እቃውን እንዳስቀመጠው የሚያገኝ ህዝብ ያለው ከኣባይ ማዶ ደብረማርቆስ ላይ ብቻ መሆኑን በደንብ ታዝቤያለሁ።ኣስቡት ስንት ማጅራት መቺ ባለባት በዚች ኣገር ውስጥ፣ስንት ኪስ ኣውልቅ ባለባት፣ስንት ራስ ወዳድ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ያክል ነው የደብረማርቆስ ህዝብ መንደር የሚያክል ገበያውን ለፈጣሪው ትቶ ወደ ምኝታው የሚያመራው።ጎጃም ኣምላኩን ካመነና ሰውን ከወደደ እንዲህ ነው።”ዋእ ጂዎርጂስ ኣለማይደል …ምን እንዳይሆን ብለህ፣የአብማ ማርያም ዘብ ሆና ትጠብቀዋለች” ይልሃል።እንዴት የስንት ሺህ ብር ዕቃህን ትተህ ትሄዳለህ ብለህ ብትጠይቀው።
ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ከኣመራሮቻችን ጋር ተጣላንና ካልገደልናችሁ ብለን ተጋበዝን።ፌደራል ፖሊስ ገባ።በጭስ ጠራርጎ ኣስወጣን።ወደ ከተማ ተሰደድን።ከተማም ተከትሎ ኣሳደደን።ጭሱ፣ዱላው፣ ዉሃ ተፈራረቀብን።ከሁለት በላይ ሆኖ በየትኛውም ቦታ ቆሞ የተገኘ ሁሉ ይወገራል።ሱቆችም፣ጠላቤቶችም ተዘጉ።ዩኒቨርሲቲ እንዳንገባ ተከለከልን።ሆቴሎች ለተማሪ ኣልጋ እንዳታከራዩ ተባሉ።እኔና ዘጠኝ የምንሆን ጉዋደኞቼ፣በረሃብና በፖሊስ ድብደባ ኣካላችን ዝሏል።ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ነበሩ።የምንሄድበት ቸግሮን ተራርቀን ማዶ ለማዶ በስልክ እየተነጋገርን እንንቀዋለላለን።በዚህ መሃል ኣንድ ጎጃሜ እናት ከላይ ከኣብማ ወደ መስጂድ የሚወስደውን መንገድ ይዘው መጡ።ችግራችንን ከዓይናችን ላይ ኣንብበውታል።ተከተሉኝ ኣሉን።ኣብረናቸው ሄድን።
ሁላችንንም ወስደው እቤት ኣስገብተው ምሳ ኣብልተው፣ጠላ ቀድተው፣ግብጦ ኣቅርበው ካስተናገዱን በሁዋላ ስለ ብጥብጡ ጠየቁን።በዝርዝር ነገርናቸው።ስለደረሰብን ነገር በዝርዝር ኣስረዳናቸው።ዓይናችንን እያየ ኣለቀሱ።[“ቡዳው” ጎጃሜ ይህ ነው ላንተ ያለው ሃዘኔታ በፍቅሩ እንድትወድቅ ያስገድድሃል]።መካከሩንና በሉ ተጫወቱ እኔ የሆነች ጉዳይ ኣለችኝ ብለውን ጠላ በገፍ ኣቅርበውልን ሄዱ።ጎጃሜ እንዲህ ነው_ከወደድህና ካመነህ፣ሳሎኑንም ጉዋዳውንም ትቶልህ ይሄዳል።ማታም ኣንድ ቤት ተሰጥቶን እዚሁ ቤት ኣደርን።ልጆቻቸውና ባሌቤታቸው ከዋሉበት ሲመጡ የለገሱን ፍቅርና እንክብካቤ እኛን የቤተሰቡ ኣባል ያስመሰለ ነበር።ስንጫወት ስንበላ ስንጠጣ ለተመለከተን ከነዚህ ሰዎች የተወለድን ነበር የሚያስመስለን።[ስንት ጉዋደኞቻችንንም ቅዳሜ ቅዳሜ ሰክረው በየምንገዱ ስንዘላዘሉ ይሰበስባቸው የነበረው ይሄው ምስኪን ህዝብ ነው።”የሰው ሃገር ሰው እንጀራ ፍለጋ እዚህ ድረስ መጥታችሁ ተቸገራችሁ” ነበር -የሚሉን ጠዋት ጠዋት ሰክረው የጠፉ ጉዋደኞቻችንን ልንፈልግ ስንወጣ]
ሰሙኑን ግን ወደ ባህርዳር በነበረኝ ጉዞ ለኣንድ ሰዓት ብቻ የነበረኝ የማርቆስ ቆይታ ሰቀቀን የሆነ ነበር።እነ ንጉስን ሰላም ብዬ ሳልጨርስ ኣስራምስቱ ደቂቃ ኣለቀ፤እነከቴ ቤት የቀረበልኝን እርጎና እንጀራ ሳልበላው ሰላሳው ደቂቃ ተጠናቀቀ፣ገና እነ ጋሽ እናውጋውን ሳላገኛቸው የቀሩኝ ጥቂት ደቂቃዎች ነበሩ።ሁሉም ላይ ኣንድ ነገር ኣለ ፍጹም የሆነ ደግነት።
ከጎጃሞች ብዙ ስጦታዎች ተቀብያለሁ- በተለይ በተመረቅሁ እለት።ኣንድ ሙሉ የግጥም ረቂቅ ተቀብያለሁ።ጎጃም አበበ (ፎጣ) ተሰጥቶኛል።ሙሉ የባህል ልብስ ተቀብያለሁ።የልምዣትንም የሰጡኝ ጎጃሞች ናቸው። ከጎጃም ከሰበስብኩት ቁሳዊ ስጦታ በላይ ግን ከልብ የመነጨው ጥልቅ ፈገግታቸው ይበልጣል።ሰሙኑንም ያየሁት ይሄንኑ ነው።ከሚሰጡኝ ስጦታ፣ከሚያስታቅፉኝ ልግስና በላይ ፊታቸው ላይ ያለው የዋህነት ይልቃል።
በጣም የሚገርመው በጣም የምወዳቸው ጉዋደኞቼ በሙሉ ከጎጃም ብቻ መሆናቸው ነው።ቆይ ጎጃም ከመሄዴ በፊት ጉዋደኛ ኣልነበረኝም እንዴ ብዬ እስክጠይቅ ድረስ የምር የምር ውስጤን የሚያውቁ ምርጥ ጉዋደኞቼ በሙሉ ጎጃሜ ናቸው።ደብረ ማርቆስ የቀራለም ልንገሬ የፊደል ገበታ፣የሰላም ደመቀ የትውልድ ከተማ፣የከተማው ኣበበ የትውልድ ቀዬ ብቻ ሳትሆን፣ለኔና ለብዙ ወዳጆቼ ድግሪ ያስጨበጠችን ብቻ ሳትሆን፣በየቤቱ ኣንድ ሼልፍ ሙሉ ግጥም የሞላባት ከተማ ብቻ ሳትሆን፣ካርቶን ሙሉ ልብወለድ በየቤቱ የሚኖርባት ከተማ ብቻ ሳትሆን፣ድምጸ መረዋ ዘፋኞች የሚያቀነቅኑባት ጉዋዳ ብቻ ሳትሆን…እኔን፣ ኤርሚን ፣ወንዴን፣ መሃመዶን፣ዮርዲን።ዋስቶን ያስተዋወቀች ብቻ ሳትሆን……የዚያ ምስኪን ህዝብ መኖሪያም ነች!!
ይህን ሁሉ ያስታወሰኝ ትዝታዬን የቀሰቀስው የሰሞኑ ጉዞ ግን ሰቀቀን ነበር።የነበረኝ ጊዜ ኣጭር መሆኑ የትዝታ ሰፈሮቼን መጎብኘት ኣላስቻለኝም።የማታ ጸሃይ የሞቅንበትን የወሰታ ሜዳን ያየሁት በሩቁ ነው፤እስጢፋኖስ ፊልምን የሰራንበትን የየራባ ጫካን ያየሁት ኣሻግሬነው፤በየአመቱ ሚያዚያ ሰላሳ ማርቆስ ሲከበር እየጠሩ ይጋብዙን የነበሩትን የእነ ትግስትን ቤት እንዳልበላሁ እንዳልጠጣሁበት በበሩ ላይ ሳልፍ በዝምታ ተውጬ ነበር።ጠላ በግብጦ ያወራረድኩበትን የኣብማ ሰፈርን ለመመልከት ቀና ስል ማየት የቻልኩት የማርያምን ቤተክርሲታን ሞገስ ነበር።ከነ ዮርዲ ጋር እርጎ የምንጠጣበትን የማዘርን ቤት ለማየት ሞክሬ ራቀኝ፤ስንት ግጥሞችን ከምርጥ ገጣሚዎች ጋር ያነበብኩባቸውን የማርቆስ ሲኒማ ኣዳራሽና የተክለሃይማኖት ኣደባባይ ዝም ብያቸው ሳልፍ ”የሰው ነገር…..” ብለውየታዘቡኝ መሰለኝ።በኣስር ብር ብቻ ከነ መሃመዶ ጋር ስንጨፍር ያደርንበትን የእየሩሳሌም ባር ዝም ብዬው ሳልፍ ”ለቺቺኒያ መሸታ ቤቶች ቀየርከኝ እንዴ” ሳይለኝ ኣይቀርም።ከፎቅ ላይ ወድቄ የታከምኩበት የማርቆስ ሆስፒታልና፣የብርሃኑ ዘርይሁን ድርሰቶችን ያጣጣምኩበት ግዙፉ ቤተመጽሃፍትም እዛ መሄዴን ከሰሙ ዝም እንደማይሉ እሙን ነው።ኣንቺ የፍቅር ሃገር ማርቆስ ስላንቺ በምን ዓይነት ቋንቋ ብጻፍ ነው ነፍስን ማርካት ሚቻለው????!!!
ጎጃም ሆይ አንቺ የነበላይ ዘለቀ፣ መንገሻ ጀምበሬ፣ ነጋሽ በዛብህ፣ ሃይሉ በለው መሰል ጅግኖች ሃገር። በነዙህ ጅግኖችሽ ታግዘሽ ጣልያን ምድርሽን ያረገጠው ቀየ ጎጃም። ፋሽስት ኢጣልያን የተዋጋው ከ80% በላይ አርበኛ ጎጃሜ ነበር።
ጎጃሜ “ቡዳ” ነው ሲትይ ሰማሁሽ
ሰውን ሰው ሲበላው የታባሽ አየሽ። ጎጃም ውስጥ ሁሉም “ቡዳ” አይባልም። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ዘራቸው ተቆጥሮ፣ በኋላ ቀር ባህል ላይ ተመስርቶ “ቡዳ” የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል። ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ጉዳይ ነው። አሁን ላይ ግንም እየቀረ ያለ ነገር ነው።
ጎጃም ሆይ ኣንቺ የሃዲስ ኣለማየሁ ኣገር፣ አቤ ጎበኛ፣ የዮፍታሄ ንጉሴ የቅኔ መንደር፣የኤፍሬም ታምሩ፣የሙሉቀን መለሰ፣ የነአበበ መለሰ የሙዚቃ ምድር፣የጌትነት እንየው፣የበውቀቱ ስዩም፣የፍቅር እስከመቃብር ስረመሰረት፣የበዛብህና የሰብለ የፍቅር መጋገሪያ………. ብቻ ኣይደለሽም።ባንቺ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የዋህ፣ኩሩ፣ቸር፣ተባባሪ ብቻ ቋንቋ ሊገልጸው የማይችል ህዝብ ለመኖሩ እኔ ምስክር ነኝ።
በያየሰው ሽመልስ

The post ጎጃሜ ቡዳ ነው ተጠንቀቁት appeared first on Bawza NewsPaper.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Trending Articles