የበረሃ ማር ——
ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ ሁለት ዓመቴ ነው:: አመጣጤም ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ስላልፈለኩ፣ በአጭሩ አሜሪካ ጥገኝነት ጠየኩ ተሳካልኝ ቀረሁ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ አሜሪካ እንደመጣሁ የዲሲ ቆይታዬን ያራዘምኩት፣ ሲጀመርም ከኢትዮጵያ ተሳፍሬ የረገጥኩት ምድር ዲሲ መሆኑ እና የመጣሁበት ዋናው ጉዳዬም እዚሁ በመሆኑ ነው፡፡ አዲስ ህይወት፣ አካባቢ፣ አየር ንብረት፣ አስተሳሰብ ጋር ለመላመድ የፈጀብኝ አጭር ጊዜ ቢሆንም ባለፍኩበት መንገድ ሁሉ የገጠሙኝን መልካም፣ አስደንጋጭና ክፉ ሰዓቶች ዛሬም እየኖርኩበት መሆኑ ያስዝነኛል፡፡
“በርግጥ ይህንን ሁሉ የሰው ክፉ ስራና አሉባልታ፣ ያለፍኩት በራሴ ጥበብ እና በአምላክ እርዳታ ብቻ ነው::
ሰዎች ለምን በእኔ ላይ ይሄንን ማድረግ ፈለጉ” ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በእኔ ላይ የሆነውስ በሌሎች ለሀገሩ እንግዳ እና ባዳ ለሆነ አዲስ ሰዎች ይደርስባቸው ይሆን?
ዲሲ ውስጥ ስኖር ካስደሰቱኝ ጥሩ ነገሮች፣ ትኩስ ሽሮና ከኢትዮጵያ በቀጥታ በአውሮፕላን ተጭኖ የሚመጣው የጤፍ እንጀራ በቀዳሚነት አስቀምጬ፣ በአጎራባቾቹ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ በትራንስፖርት፣ በንግድ ቦታዎች፣ ሬስቶራንቶች የሃገሬን የኢትዮጵያን ልጆች በተለያየ የሞያ ዘርፍ ተሰማርተው ሳይ ያስደስተኛል፡፡
አንዳንድ ጊዜም ባደኩበት አርባ ምንጫ ከተማ ያለሁ እንጂ ብዙ ሽህ ኪሎ ሜትር አቋርጬ በስደት እንደምኖር ረሳለሁ:: ብዙ ኪሎ ሜትር፣ ጋራ፣ ሸንተረር፣ ሃይቅ
ተጉዞ ከቋንቋ፣ ከባህል ተራርቆ ሲኖር በበአድ አገር እንደ እኔው “ሰው ይርበው ይሆን?” ብለህ በቋንቋህ የምትሰጠው ሰላምታ በጥሩ ጎኑ ባይታይብህም፣ እኔ
ግን ዛሬም ልማዴን አልተውኩም፡፡ አንዳንዴ ባላየ ስትታለፍ፤ ሌላ ጊዜም በቁጣና በግልምጫ፣ ከቀናህ ገሮቹ በፍጥነት ከፈገግታ ጋር የታጀበ ሰላምታ ይሰጡኻል፡፡
በአሜሪካ(ዲሲና አካባቢው) የሚኖሩ አንዳንድ ሃበሾች አያቴን ያስታውሰኛል፡፡ አያቴ አልፎ አልፎ ከምትኖርበት ገጠር ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ምንኖርበት አርባ ምንጭ ልትጠይቀን ትመጣለች፡፡ ከመጣች እለት ጀምራ ግን ወደ አገርዋ የምትመለስበትን ቀን ትናፍቃለች፣ ትቆጥራለች፡፡
በፍጥነት ወደ ሀገሯ ለመመለስ ከምታቀርባቸው ምክንያቶቿ መካከል ”ከብቶችን ጅብ እንዳይበላቸው፣ ሰንበቴ ሳላወጣ ተራዬ እንዳያልፍ፣ እድር የመክፈያዬ ቀን ሊያልፍብኝ ነው” የመሳሰሉት ናቸው፡፡
“እመዬ ለምንድን ነው ግን ከመጣሽ ቀን ጀምሮ ለመመለስ የምትቸኩይው” ብዬ ስጠይቃት “አንዳንድ የከተማ ሰው ክፉ ነው” ትለኛለች፡፡
“ቤቱን ዘግቶ እየበላ፣ ሌላው ይቅርና ለእግዜር ሰላምታ እንኳን መልስ ለመስጠት ይቸገራል፡፡
እንዴት ዋልክ? እንዴት አደርክ? ሲባል ‘እግዚአብሄር ይመስገን’ ብሎ ለመመለስ ጉንጩን ይደክመዋል::
ምን አለ፣ አይከፈልበት፣ አጸፋ ቢሰጥ” ትላለች፡፡ አዲስ ስትሆን በራስህ ወገኖች ጉልበትህ ይበዘበዛል፣ መንገዱና አቅጣጫው እንደተሰወረብህ ከታወቀ “ይሄ የስህተት መንገድ ነው፡፡ ና! ይሄ ነው ትክክል” አትባልም፡፡ የምትቀማው ገንዘብህን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብህንና ማንነትህን ነው፡፡
በዲሲ፣ ሜሪ ላንድ፣ ቨርጂኒያ አካባቢ የሚኖሩ ስፓንሾች፣ ሶማሌዎች፣ የሌላ አገር ዜጎች መተሳሰብ እና መደጋገፍ የሚያስደንቅ ነው፡፡
The post ሀበሻን ፍለጋ appeared first on Bawza NewsPaper.