ጃንሆይ ስለ ሰጡኝ ሳንቲም ታሪክ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በልጅነቴ ስድስት ኪሎ አካባቢ ጃንሆይ በመኪናቸው ሲያልፉ እጅ ስንነሳቸው አንዳንዴ ውሪው ካልበዛ በብር የተሰራ እታች የሚታየውን ምስል ያለው ሳንቲም በፈገግታ ያድሉን ነበር።
ያ እድል አንድ ቀን አጋጥሞኝ እኔም ጠጋ ብዬ ተቀበልኩና ፣ አዲስ የሆነው ሳንቲም ብርቅርቅርቅ ሲል ዱርዬዎች እስኪ አሳየን ብለው ቀረብ ሲሉኝ ሃሳባቸው ገብቶኝ ቶሎ ኪሴ ከትቼ እንደ ንፋስ ወደ ቤቴ ሮጥኩ። እያለከለኩና ላብ እያጠመቀኝ ትንፋሼ ቁርጥ ብሎ ከቀማኛ ያዳንኳትን ሳንቲም ላወጣ እጄን ኪሴ ስከት ባዶ ሆኖ አገኘሁት። ድንገት በሌላኛው ይሆናል ብዬ ልቤ በድንጋጤ ተሞልቶ ሌላኛው ኪስ ዘው ቢል ላጲስ ተገኘች። አንደገና በእርግጠኛ ያስገባሁባት ኪስ እጄን ልኬ ከፍተኛ ምርመራ ሳካሂድ ሌባ ጣቴ ጉዴን ነገረችኝ። እንኳን ሳንቲም የረሳሁት ብርቱካንም ቢሆን የሚያሳልፍ ትልቅ ቀዳዳ እጄም ጭምር አልፎ ጭኔን አገኘ። በንዴት እንዴት ወደላይ ካለመንደርደር ዘልዬ ወደመሬት ከታላቅ ጩኸት ጋር ዘፍ አልኩኝ። ገና ቤት መድረሴን ያላወቀች እናቴና ብዙ ሰራዊቷ ኡኡኡ እያሉ ከቤት እየበረሩ ወተው ፣ አፈር ላይ እምባዬን እየዘራሁ ከምንደባለልበት ማን መታህ እያሉ ወንዶቹ ዱላ እየመዠረጡ በጥይት እንደቆሰለ ሰው በሸክም ወደ ቤት አስገቡኝ። አገላብጠው ቢያዩኝና ቢመረምሩኝ ከለበስኩት ትቢያ ሌላ ምንም ቁስል ስላላዩ ፣ ተረጋጉ። እኔም ንዴቱ በራሴ በመሆኑ ተነስቼ የገዛ ራሴን በሁለት እጄ መቀጥቀጥ ስጀምር ፣ እናቴም ሌሎቹም አእምሮው ተነክቶ ነው ብለው ፣ አባ ይጠሩ ፣ ጠበል ይምጣ እየተባለ ግጥም አድርገው ሲይዙኝ ነገሩ ገርሞኝ ማልቀሱ ቀርቶ መንከትከት ጀመርኩ። ይሄም እራሱ በጣም ስላስደነገጣቸው እንዲለቁኝ ሁኔታውን እንደ መትረየስ ቃላትን እያጋጨሁና እያዳፋሁ አስረዳሁ። እናቴ ነገሩ ሲገባት እምባዋ እስኪፈስ ተንከተከተች ፣ ሌሎቹም ተከተሏት። እኔም ተረጋግቼ እምባዬን ጠራርጌ ወደተዘጋጀልኝ መክሰሴ ዞርኩ።
የዚህ ትምሕርት ፨፧ ከኪስ ቀዳዳ ፣ ያስተሳሰብ ቀዳዳን ፍሩልኝ።
The post When I was received money from King Haile Selassie I ጃንሆይ ስለ ሰጡኝ ሳንቲም ታሪክ appeared first on Bawza NewsPaper.