ስለ ፍቅር! !!!!
ፍቅር ሰውኛ ነው ። ዘሩም ሃይማኖቱም ሰው መሆን ብቻ ነው ። የሰው ልጅ ስለ ሰው መሆን ብሎ ሰውኛ የመዋደድና የመተሳሰብ እሴቶችን ያስቀድማል ። ለሰው ለማዘን ወይንም ለሰው ለማሰብና ከሰው ጋር በሰውነት ደረጃ ለመኖር ሃይማኖተኛ መሆን ቅድመ መስፈርት አይሆንም ። እንደ ሰው ለመኖር ሰው መሆን በቂ ነው ። የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚጋራቸው ግዙፍ እሴቶች ሞልተውታል ። ሃይማኖት አብሮ ለመኖር ብቸኛውና ምትክ የለሽ ዋስትና ቢሆንማ ኖሮ ከግማሽ ህዝባቸው በላይ ኢ አማኒ ((ሃይማኖት የለሽ) ) የሆነባቸው የእስካንዲቪኒያ ሃገራት በእድገትና በሰላማዊነት ብሎም በደግነት ረድፍ ባልተገኙ ነበር ።
ያደግኩበት ማህበረሰብ የዘር የሃይማኖት ልዮነቶች ቢኖሩትም እንደ ሰው የሚጋራቸውን ስሜቶችና ፍላጎቶች አጉልቶና አስፋፍቶ መኖር ይችልበታል ። በልጅነቴ ሰውን ከመውደዴ የተነሳ ስለ ባልንጀሮቼ ፍቅር ስል እኔን የማይጎዳ እነርሱን ግን የሚያስደስት ነገር ፈጽሜያለሁ ። ያደግኩበት ሰፈር የሙስሊሞች ሰፈር በመሆኑ በረመዳን ጾም ጊዜ ባልንጀሮቼ ሲጾሙ ከነርሱ ፊት መብላት የነሱን ረሃብ መቀስቀስ እንዳይሆንብኝ በሚል ንጹህ የልጅነት እሳቤ ተነስቼ በጾም ወራት ከፊታቸው ላለመመገብ ጥረት አደርግ ነበር ። የልብ ጓደኝነቴን ለማሳየት ረመዳንን አብሬያቸው እጾም ነበር ። አብሮነቴንና ጓደኝነቴ የሚያስከፍለው ዋጋ ካለ የመስዋእትነት ፈቃጀኛነቴን ለማሳየት የባልንጀራነት ቁርጠኛነቴን ለማሳየት በትንሹ ስጾም እውላለሁ ። የመውሊድ ቀን ሁላችንም የወልዲያ ክርስቲያን ልጆች ከሙስሊም ወንድሞቻችን ጋር ዳንዮል አወል መስጂድ በሚደረገው የጸሎት ስርአት ላይ ዳና ዛውያው ስር እንገኛለን ። ባልንጀሮቻችን ሲደሰቱ አይተን እኛም ደስ ይለን ነበር ። ይህንን ቅን ድርጊታችንን ከሃይማኖት አንጻር ማየቱን ተውትና ቢያንስ ቢያንስ ትላልቅ ሸኪዎች በአባትነት ሲመርቁን አሚን እንላለን ። መልካም ምኞት ከጤናማ ማህበረሰብ የሚመነጭ ነውና ሰውኛ ዋጋችንን ይጨምራል ። የመረቀኝን ሽማግሌ የምርቃን ንያው እንጅ ሃይማኖቱ አያሳስበኝም ነበር ። ሃይማኖታችን ቢለያይም ሰው የመሆናችንን የጋራ ጸጋ የሚያጎሉ ስርአቶች የግድ ከሃይማኖት ጋር ብቻ የሙጭኝ ብሎ ማላዘን ከሰውኛ ሚዛን ማጉደሉን ደጋጎቹ አባቶቻችን አስተምረውናል ።
እንደነገርኳችሁ በየጁ ዳና ምድር በሚደረገው ስርአት ላይ ጓደኞቻችንን አጅበን መሄድ የባልንጀራነት ሃቂቃን እንደመወጣት እንቆጥረው ነበር ። ያኔ በልጅነቴ የመውሊድ ቀን በዳና ምድር ሲከበር እንደስከዛሬው ሳይሆን ጉዞው በእግር ስለሆነ ሙስሊም ወንድሞቻችን ብቻቸውን እንዳይሆኑ ጉዞና ዚያራቸውን ለማሳለጥ አብረን እንተም ነበር ። ጓደኞቻችን ጋር አብረን ስንጓዝ የሚመለከቱ ሙስሊም አባቶቻችን ከጓደኝነት በረካ አይለያችሁ! !! እያሉ ሲመርቁን አጥንታችን ይለመልም ነበር ። ይህንን ያደረግነው ለእምነቱ አምልኮ አልነበረም ። ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን ጓደኝነታችን ላይ የአብሮነት እሴት ለመጨመር እንጅ ። የመስቀል ቀንም ቢሆን ሙስሊም ጓደኞቻችን ለአምልኮ ሳይሆን የእኛን ደስታ ለማየት አብረውን ይሆናሉ ። አብሮነትና ጓደኝነትን ከአምልኮ ነጥለው የሚያስቡ ስለመሆናቸው ምድሩም ሰማዩም ይመስክር ። በየጁ ምድር ዛሬም ድረስ ይህ ደማቅ እውነት ህያው ሆኖ በዳንዮች ምድር ላይ ቀጥሏል ። አሁንም ዳና ምድሩ ይመስክር ። ታዲያ ይህንን ያደረግነው ተገደን ነው እንዴ? ?? ይህንን የኖርነው ሙስሊሞች አስገድደውን ነው እንዴ? ?? ኧረ ጎበዝ የቀመስነውንና የዳሰስነውን እውነት አየር ላይ በተንጠለጠለ ምኞት ልታስጥሉን አትሞክሩ ። እኛ በደጃችን የቀመስነውን ወጥ ጣእሙን ልትነግሩን ስትሞክሩ ትንሽ ይክበዳችሁ እንጅ! !!!
Mengistu Zegeye Facebook page
The post ስለ ፍቅር! !!!! appeared first on Bawza NewsPaper.