Quantcast
Channel: Bawza
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

እሬቻ!

$
0
0

እሬቻ

ቢሸፍቱ አደይ አበባ ለብሳ ጥንታዊውን የጥቁር ህዝቦች እሴት የምታሳይበት ለጥቁር አምላክ ምስጋና የሚቀርብበት ክረምቱ ማለፍ ብርሃን መፈንጠቁ በአደባባይ የሚታወጅበት ልዩ ቀን ነው፡፡ 
በእሬቻ ዋዜማ የሐይቆቹ ከተማ እንደሌላው ቀን ቶሎ አይነጋላትም፡፡ የገላን ኮረብታዎች፣ የጭቋላ ከፍታዎች፣ የየረር ሰንሰለታማ ተራራዎች ቁልቁል ቢሸፍቱን እያዩ ሐሴት የሚያደርጉበት ቀን ነው፡፡ ኢሬቻ የዛሬ አይደለም፤ ጥንታዊ የአባይ ሸለቆና መሰል የኦሮሞ ሕዝቦች ዘንድ ፈጣሪ አምላክ /ዋቃን/ ለማመስገንና ምልጃ ለመጠየቅ የሚከናወን የጥንት ሥርዓት ነው፡፡ 
የኢሬቻ ሥርዓት በተለያዩ ቦታና መልክ የሚከናወን ሲሆን ጠቅለል ባለ መልኩ ግን በሁለት ቦታና ወቅቶች ይከፈላል፡፡ አንዱ በተራራ ላይ የሚከናወነው የኢሬቻ ስርዓት ሲሆን ሌላው ቢሸፍቱ የምታስተናግደው በጅረትና ሀይቆች ዙሪያ የሚፈፀመው የኢሬቻ ሥርዓት ነው፡፡ ኢሬቻ ቱሉ (በተራራ ላይ የሚፈፀም ኢሬቻ) በተራራ ላይ የበጋ ወራቶች አልፈው በበልግ ወቅት መግቢያ ላይ የሚከበር ነው፡፡

ታህሳስ ጥርና የካቲት ወራቶች ከፍተኛ ፀሀይ የሚታይበትና የውሀ እጥረት የሚከሰትባቸው ወራቶች ሲሆኑ በእነዚህ ወራት ሰውም ሆነ እንስሳት በውሀ እጦት በእጅጉ የሚጎዱባቸው በመሆኑ ፈጣሪ /ዋቃን/ ዝናብ እንዲያዘነብላቸው የሚጠይቁበት ባህላዊ የኢሬቻ /የምስጋና/ ጊዜ ነው፡፡ ቦታውም የደመና መገናኛ ርጥበት በተቸረው ተራራ ጫፍ ሲሆን የፀሎትና ምልጃ ልመናን በባህሉ መሰረት ለዋቃ ያቀርባሉ፡፡

ቢሸፍቱ በመልካ ጅረቶች ላይ የሚደረገውን የኢሬቻ ሥርዓት የምታስተናግድ ከተማ ናት፡፡ የክረምቱ ወራት አብቅቷል፡፡ መስከረም ተጋምሷል፡፡ ጨለማ አልፎ ብርሃን ሆኗል፡፡ በአንድ ቦታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው የሚያከናውኑት የኢሬቻ ሥርዓት በምስራቅ አፍሪካ ምናልባትም በአፍሪካ ትልቁ ኩነት ነው፡፡ 
ኢሬቻ የብራ በዓል ነው፡፡ የሐይቆች ሀብታም የሆነችው ቢሸፍቱ ቅንጡ ሆቴሎቿ ሳይቀር ቄጤማ የሚጎዘጎዙበት አደስ አደስ የሚሸቱበት ቀን ነው፡፡ አየሩ በአርቲ ሽታ የሚታወድበት፤ ፈረሶችና በቅሎዎች ተንቆጥቁጠው ከጌቶቻቸው ጋር ወደ ሆራ አርሰዲ የሚወርዱበት ልዩ ቀን ነው፡፡ የአድአ ጅረቶች ዛሬስ እንደ ሆራ ባደረግን ብለው የሚቋምጡበት፤ ሆራ የያዘው የውሃ መጠን ቀለም ቢሆን የዚህ ቀን የምስጋና ዜማ፣ የዚህ ቀን የደስታ ስሜት ቢጻፍበት ቀለምነቱ ባልበቃ፤ ተራራዎችና መስኮች በአዝርእትና በአበባ ተሸፍነዋል፡፡

ገበሬ አርብቶ አደር ተስፋ ያደረገው አዲስ ወር ነው፡፡ ለዚህ ቀን በመድረስ ከደስታና ለዋቃ ከሚቀርብ ምስጋና በቀር ምንም የሚሰጥ ሌላ የሚተካከል ስጦታ የለም እናም ቢሸፍቱ በባህላዊ ዝማሬ በምስጋናው ቀን ነገ ትደምቃለች፡፡ ውሀ የህይወት ሁሉ ምንጭ ነው የሚለው የኦሮሞ ቀደምት ፍልስፍና ፈጣሪን ስለ ግሩም ስራው ለማመስገን “ዝናብ ሰላምና ትውልድ ” እንዳላቸው ልዩ ፋይዳ ኢሬቻም በቢሸፍቱ በሆራ ሐይቅ ዙሪያ የሚከናወን የምስጋና ቀን ባህላዊ ክንዋኔ ነው፡፡ 
ቢሸፍቱ የዘንድሮን እሬቻ ለማየት ጓጉታለች፡፡ ታላቁን ኩነትም በድምቀት ታስተናግዳለችና፡፡
ይህ ድንቅ ባህል እስከዛሬ ራሱ በአለም ቅርስነት አለመመዝገቡ ይገርማል አሁንም ለነገም መባል የሌለበት ነው፡፡

Atsebha Abay
 

The post እሬቻ! appeared first on Bawza NewsPaper.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Trending Articles