ወቅቱ አስቸጋሪ በመሆኑ የታዴን ለቅሶ መድረስ ለምትፈልጉ ሰኞ September 7 ና ማክሰኞ September 8 ከሰአት በኋላ ከ 2 pm እስከ 8 pm በ 5380 Eisenhower Avenue, suite C Alexandria VA እንቀመጣለን ። የቀብር ስነስርኣቱ ደግሞ ሀሙስ September 10 ከ ሰአት በኋላ ከቀኑ በ 1 : 00 pm 9902 Braddock Rd, Fairfax VA 22032 ይፈጸማል ። ወቅቱ የሚጠይቀውን ጥንቃቄ በማድረግ ታድዬን በፍቅር እንድንሸኜው እለምናችኋለሁ።
ስለዚህ ባለሙያ አንጋፋዋ የጥበብ ሰው አለምፀሀይ ወዳጆ ለክብር ቀኑ የሚከተለውን አስፍራ ነበር።
ዕውቁ መራሔ ጥበብ ታደሰ ወርቁ ከትልቅ ቤተሰብ ከደጃዘማች ብዙነህ በዛብህ ልጅ ከወ/ሮ ወደርየለሽ ከሚወለዱት እናቱ ከወሮ የሺሐረግ ወ/ አረጋይና ከግራዝማች ወርቁ ባልቻ በከፋ ክፍለ ሀገር ሚዛን ተፈሪ የሁለተኛ ጋብቻ የመጀመሪያ ልጅ ሆኖ እንደ ኢትዮዽያ አቆጣጠር ጥር 23 ቀን 1942 ዓም ተወለደ::
እናቱ ከመጀመሪያ ትዳራቸው ከአቶ አስፋው እጅጋየሁንና ግርማን ወልደው ነበርና ለእናቱ ሦስተኛ ልጅ ሆኖ ተቆጠረ:: መጋቢት 3 ቀን የባታ በዓል ሲከበር የታደሰ ወርቁ ክርስትና ተደግሶ ለቤተሰቡ የቅርብ ወዳጅ ለሆኑት ለደጃዘማቸ አለማየሁ ፍላቴ ተሰጥቶ ክንፈ – መድህን ተሰኘ:: ወ/ሮ የሺሐረግ በተከታታይ አሰለፍን መርዬን ከወለዱ በኋላ በቤት ውስጥ የነበረው ሰላም ደፈረሰ፡፡ ደጃዝማች አለማየሁ ፍላቴ ሁለቱን ልጆች ማለትም ታዴንና አሰለፍን አዲስ አበባ ወስጄ ላስተምር ብለው ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ እነሱ በት/ቤት እያሉ በእናትና ልጆች መሀከል ያለው ናፍቆትና መፈላለግ በማየሉ የደ ለወ/ሮ የሽመቤት ጉማና በወቅቱ ለፊታውራሪ አለማየሁ መመለሻ በተዘጋጀው አውሮፕላን ውስጥ ሸኚ በመምሰል የተገኙ ወ/ሮ የሺ ሐረግ ከአውሮፕላኑ አልወርድም ብለው በማስቸገር ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ በአማቻቸው በወ/ሮ ወደሬ ቤት ጠቀምጠው ልጆቻቸውን እየተመላለሱ መጠየቅ ያዘወትሩ ስለነበር ከእለታት ባንዱ ቀን ግብር ገብቶ እራት ተበልቶ ካበቃ በኋላ ደጃዝማች እረፍት በማድረግ ላይ እንዳሉ ወ/ሮ የሺሀረግ የተኛውን ልጃቸውን ታዴንና አሰለፍንም ጨምረው ሰርቀው ድሮ ዶቅዶቄ ወይም ኩርኩር በምትባል መኪና ኮንትራት ይዘው ጠፉ የተኮናተሩትን መኪናም መንገድ አቁመው ፀጉር ቆራጭ ቤት ጎራ ብለው አሳምረው ይዘውት በመሄድ ከአያቱ ከወ/ሮ ወደር የለሽ ቤተሰብ ተደባለቀ፡፡ሚዛን ተፈሪ ውስጥ በወላጆቹ የተሰራችው ሚካኤል ቤተክርስቲያን አለ፡- በቤት ውስጥ በእንክብካቤ የሚያሳድገው ለማ የተሰኘው ግለሰብ በበቅሎ እየወሰደው በዚህ ቅጥር ግቢ የሚያሳልፈው የልጅነት ትዝታ ነበረው፡፡የእሱም ሆነ የእናቱ ደስታ ወደር አልነበረውም፡፡ በኋላም ወ/ሮ የሺሐረግ ባለብዙ ንብረትና ሐብት ባለቤት የነበሩትን አቶ ከበደ ደገፋን አግብተው መርካቶ ወሰን ሰገድ አጠገብ መኖር ሲጀምሩ አሰግድ በዬ አዛልና ኤልሳ ተወለዱ፡፡መዝለልና መጫወት የሚወደው ታዴ ከት/ቤት እየቀረ ውሎው በቀለ ወያ ሜዳ ሆኖ የኳስ ጫወታ ፍቅሩ ከኪነ ጥበብ ፍቅሩ ማየሉን ከልጅነት ጀምሮ ላስተዋለ ” አንዴት ሙያውን ቀየረ ?”የሚያሰኝ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ወቅት ነው ትምህርቱን በወግ እንደማይከታተል የተገነዘበው 50 አለቃ ታምሩ በወታደርነት ወደሚሰራበት ወደ ፖሊስ ሰራዊት ይዞት የሄደው የክርስትና አባቱን የሚያውቅም ቤተሰብ በፅህፈት ስራ እንደቀጠሮ ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የተሰጠው መክሊቱ በሰው የሚወሰን ባለመሆኑ ታዴ ከሌሎች አስር ሰዎች ጋር ወደነበረው የሙዚቃ ክፍል ተወሰደ፡፡ የቅጥር ፎርም መሙላት እንደነበረበትም ባለማስተዋሉ ይመስላል፡ እስክሪብቶ እጁ ላይ አልነበረም፡፡ ዘፈኗን ተለማምዳ እረፍት ላይ የነበረችው ተወዳጇ ድምፃዊት ሒሩት በቀለ አውሳው በተውሶ ስክሪብቶ በሞላው ቅፅ ተቀጥሮ ክላርኔት መጫወቱን ተያያዘው፡፡በወቅቱ የፖሊስ ኦርኬስትራን የዳንስ ቡድን የሚያሰለጥነው ሽፈራው ከበደ ስለነበር ከእሱ ሥር በመሆን ይመለከት ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደነሰ በመቀጠልም አሰልጣኝነቱን ተረከበ፡፡ታዲያ የታዴ የሙዚቃና የውዝዋዜ እድገት እየጨመረ ሲሄድ ሴቱን በፍቅር የማማለል ባህሪውም እንዲሁ እየጎለበተ ሄዶ እሱን እራሱን ስራ ለማስያዝ ደፋ ቀና የሚለው ታምሩ ቤትም ተጠርጥሮ ነበር መሰል የሰፈር ልጆች መንገድ ላይ ቆመው ይገጥሙበት ነበር ” ………… ቆርቆሮው ኳኳግቢውም ኳኳኳ…ታምሩ ሲሄድ ታድዬ ተካ” ይሉት ገቡበአለባበሱም ቢሆን በኪሱ ውስጥ ምንም ገንዘብ ባይኖረው እንኳን ፅድት ያለ ውብ አለባበስ እንዲለየው ከቶም አይፈቅድም ነበር:: ቆንጆና ውብ ነገር መልበስ መውደዱን ጠንቅቆ የሚያውቀው አብሮ አደግ ጏደኛው ዕውቁ ድምፃዊ መልካሙ ተበጀ በደርግ ዘመን ዩኒፎርም መልበስ ሲታዘዙ ” አይይ ታድዬ መሬት ሲታወጅ አንተን አይመለከትህም ቤት ቢወረስም አንተን አይመለከትህም አሁን ግን በአለባበስ ስለመጡ ያንተ መሰደጃ ሰዓት አሁን ነው …. ” ብሎ ቀልዶበታል::በፖሊስ ኦኬስትራ ውስጥ በሚሰራበት ወቅት ላይ እያለ ችሎታውን የተገንዘበው አበራ ፈይሳ የዳዊት ሙዚቃ የወጣት ሙዚቀኞች ክፍል ባልደረባ አባል ነበርና ታዴን ይዞት ወደብሔራዊ ቲያትር በእንግድነት ጋብዞ ይዞት ሔደ ፡፡ በአንጋፋውና ዕውቁ አውላቸው ደጀኔ የሚሰለጥነው የቲያትር ቤቱ የባህል ቡድን ለዓለም አቀፍ ዝግጅት ተሳታፊነት ያጠናውን ትርኢት ለ5 የወቅቱ ሚኒስትሮች ያስገመግም ነበር፡፡ የአዳራሹ መብራት የግቢው ፅዳት ፣ የአካባቢው ድባብ ፣ የመድረኩ ስፋትና ውበት የታዴን ልብ አስረቅርቆ አይኑን በእንባ ሞላው፡፡ ተገረመ ፣ ተደነቀ :: በእንደዚህ አይነት መድረክና ከእንደዚህ አይነት ሙያተኞች ጋር የመስራት ዕድል አገኝ ይሆን ? በማለት እራሱን ጠየቀ፡፡ ያቺ ቀን ናት የታዴን መጪ ህይወት ጥያቄ ያጫረችው ! እንደተመኘው አልቀረም ቅጥሩ ፀንቶ ሲመጣለት የዘመናዊ ክፍሉ ተወዛዋዥ በመሆን ነበር የተቀጠረው የክፍል ሀላፊው ሌላው ሁለገቡ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ሣህሉ ባልተመቻቸው ቀንና የጀመሩትን ስራ እንዲጨርስ በመደቡት ግዜ ታዴ ውዝዋዜ ማሰራቱን ተያያዘው፡፡ውስጡ ያለውን ችሎታ ለማየት የቴአትር ቤቱ የወቅቱ አስተዳዳሪም ጊዜ አልፈጀባቸውም::መቼም እንደሚታወቀው የቀድሞው ቀዳማዊ ኋይለስላሴ ትያትር ቤት ከውጭ አገር በሚመጡ የተውኔት የሙዚቃና የዳንስ አሰልጣኞች ከመታደሉም ሌላ የተሳታፊ አርቲስቶችም አልባሳትና ጌጥ ሜካፕና ቁሳቁስ ከተለያዩ ዓለማት ይመጡ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚም ዕውቋ የሜክሲኮ የዳንስ አሰልጣኝ አና ሜሪዳን ተገኝታ ነበርና የቴያትር ቤቱን ተወዛዋዦች የዳንስ ችሎታና ዕውቀት እጅጉን ከፍ አደረጋቸው፡፡ በተለይም ታዴ ዘወትር እንደሚያነሳት ሁላ በውስጡ የነበረውን የዳንስ ጥበብ እይታ በጣም በእመርታ አሳደገችለት:: በወቅቱ በቴአትር ትወናም በውዝዋዜም በሁለቱም ሙያ በጋራ መሳተፍ የተለመደ ነበርና የኢትዮጵያ ፈርጥ ባለሙያዎች እነአስናቀች ወርቁ እነጠለላ ከበደ እነጀምበሬ በላይ ….. ወዘተ አብረው መድረኩን አስዉበውት ነበር፡፡ እያደርም የታዴ ችሎታና ልምድ እያየለ ሄዶ የክፍል ኋላፊነቱን መያዝ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ለመሳተፍ በቃ፡፡ ከሜክሲኮና ከአልጄሪያ ፌስቲቫሎች ተሳትፎ ከተመለሰ በኋላ ታዴ በተውኔቱ መድረኩም በትወና መታየት ጀመረ፡፡የሥርዓት ለውጥ ተካሂዶ አዳዲስ ትርኢቶች በዓይነታቸውም በቁጥራቸውም እየጨመሩ ሲመጡ “በእናት ዓለም ጠኑ ” ላይ በላይ ዘለቀን በመሆን ” በዋናው ተቆጣጣሪ “፡- ዳኛውን “በአሉላ አባነጋ ” አጋፋሪውን” በመሆን ተጫወተ፡፡የዓለም አቀፍ የጥቁሮች በዓል በናይጄሪያ ዋና ከተማ በሌጎስ ሲካሄድ ” ትግላችን ” የተስኘውን የመጀመሪያውን ሙዚቃዊ ዳንስ ድራማ ከሌለው ድንቅ ባለሙያ ከሃይማኖት ዓለሙ ጋር በመሆን አዘጋጀ :: ከዚያ በኋላ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያን የዳንስ እንቅስቃሴ ጥበብ ባልተለመደ መልኩ ደረጃውን አሳምሮ ቀየረው፡፡ ለወጠው፡፡የሚቀርቡት እንቅስቃሴዎች በሙሉ በአልባሳት – በወግ ዕቃ -በጌጣጌጥ ከመዋባቸው በላይ ምክንያታዊ እንቅስቃሴዎችና ትርጉም ሰጪዎች እንዲሆኑ አደረገ፡፡ በየሙዚቃው እሪትም የተወዛዋዡ ሰውነትና እንቅስቃሴ እንዲታሰር በማድረግ ከተወዛዋዦቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሙዚቃ ፈጣሪዎችና አቀናባሪዎች ጋር አብሮ መስራትና ማጋመድ ጀመረ፡፡ ባልተለመደ መልኩ ጉልበታም ስራዎችን አቀረበ፡፡በቴአትር ጥበብም በዝግጅት ድንቅ ባለሙያ ሆነ፡፡ “ትግላችን ” “ትግል ነው ፣ መፍትሔው ፣ ” ” ፍልሚያ ፣ ” “አምታታው በከተማ” ን አዘጋጀ :: በማከታተልም ለዓለም አቀፍና ለሀገር አቀፍ ዝግጅቶችና ለውጭ እንግዶች የሚሰሩ ስራዎችን እንዲመራና እንዲያስተባብር በተከታታይ ይታጭ ገባ፡፡ በተለይ “ደማችን ” የተሰኘውን ሙዚቃዊ ዳንስ ድራማ ከ100 በላይ በሚሆኑ የአራት ቴአትር ቤቶች ባለሙያዎች ( ማዘጋጃ ቤት ፣ ሀገር ፍቅር ፣ ብሔራዊ ቴአትርና ራስ ቴአትር ) ከተውጣጡ ምርጥ ባለሙያዎ ች ጋር የሰዓት እላፊ የፈቃድ ወረቀት አስወጥቶ እስከ ለሊቱ ፣ ሰባት ሰዓት ማለትም በቀን እስከ 15 ሰዓት በማሰራት ድንቅ የጥበብ ውጤት አበረከተ፡፡በተወዛዋዦችና በባለሙያዎች ህሊና የማይፋቁ – ከሙዚቃ ባለሙያዎች ልቦና የማይጠፉ ከተመልካቾች ትውስታ የማይርቁ ሠራዎችን በተደጋጋሚ አቀረበ፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱና የተጓዘበት ስፍራ ታሪኩን ከፍ አድርጎት እስከዛሬ ድረስ በመላው ኢትዮጵያዊ አእምሮ ተቀርፆ ከፍተኛ የኩራት ስሜትን የፈጠረው “የሕዝብ ለሕዝብ” የሀገረሰብ ሙዚቃዊ ቅንብር ልዩ ሥፍራን አስያዘው፡፡ ታዴ ይህንን ስራ በኋላፊነት ከመምራቱ በፊት የካሜራ የቪዲዮና የስዕል እውቅ ባለሙያዎችን ይዞ በኢትዮጵያ የገጠር መንደሮች በመዘዋወር የየብሔረሰቦችን ጭፈራና ዜማ በመቅረፅ ጌጣቸውን አለባበሳቸውን አኗኗራቸውን እንዲሁም የአካባቢውን ገፅታ መዝግቦ በማምጣት ለሥራው መንደርደሪያ አበጀ፡፡ ያንንም ያጠናውን ጥናት ወደመድረክ በማምጣት የማይጠፋ አሻራውን አሳረፈ፡፡በዚያን ወቅት ነበር አጋጣሚውን በመጠቀም ከሚዛን ተፈሪ በለቀቀ በግምት ከ40 ዓመታት በኋላ ወደትውልድ ሥፍራና መንደሩ ያዘገመው :: በጣም ተቀያይሮ ተለውጦ ጠበቀው፡፡ ሰፈርተኛውን እየዞረ ያሳደገውን ለማን ለማየት ተማፀነ፡፡ ቤቱን አሳዩት ተኝቶ የነበረው ለማ ሰው እንደሚፈልገው ተነግሮት ሲወጣና ታዴን ሲያየው ለጥቂት ደቂቃ እንኳን ሳይጠራጠር “ታድዬ” ብሎ አቅፎ ሳመው :: እየተላቀሱ ወደአባቱ መኖሪያ ቤት ተያይዘው ሄዱ፡፡” የሕዝብ ለሕዝብ ” ትርኢት ከመሰረተ ሀሳቡ መፀነስ ጀምሮ በእያንዳንዱ የሙዚቃ ሕይወትና አሰራር በመድረኩ ላይ በቀረበው እንቅስቃሴ አልባሳት ጌጣጌጥ የመድረክ ሲናሪ የዚህ ሙያተኛ የታደሰ ወርቁ ድካምና ፈጠራ ነው፡፡ ይህንንም አብረው ጥበቡን የሠሩት ባለሙያዎች በሙሉ ሁሉም በሕይወት ኖረው በእንባ እየተራጩ መመስከራቸው ትልቅ ነገር ነው:: ስህተት ኖሮ ቢሆን በጥፋቱ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚገባው ሁሉ ሥራው ተዋጥቶ ሲደነቅና ሲሞገስም አብሮ መደነቅና መሞገስ ያለበት ታደሰ ወርቁ ነው፡ : የኢትዮጵያውያንን የጥበብ ሀብት ጉልበት ያሳየ ሥራ ለመሆኑ ሁሉም ይመሰክራል፡፡ ወደ ሀገሩም እንደተመለሰ በየግዜው ጠይቆት የነበረው የሙያ ስልጠና ትምህርቱ ጉዳይ መልስ ባለማግኘቱ የሚወዳቸው እናቱን አንድ ልጁን ሀገሩንና መድረኩን በእንባ ተለይቶ ርቆ ሰሜን አሜሪካ ተቀመጠ ፡፡ ከረዥም ዓመታት ቆይታ በኋላ በዶ.ር ዮናስ አሰባሳቢነት በስደት የሚገኙ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ከአዳዲስ ወጣቶች ጋር በተወሰኑ ከተሞች የጥበብ ውጤቱን አቀረበ፡- ከሙያና ከጥበብ ፍቅርና ችሎታ መሳ ለመሳ በሰው አክብሮቱና መወደዱ በቸርነቱና በጥሩነቱ በለጋስነቱ በትህትናው የሚታወቀው ታዴ ከግለሰብ እስከማህበረሰብ ያልረዳውና ያልደገፈው የለም፡፡አብያተክርስቲያናትን ማህበራትን ተቋማትን በሙያ በገንዘብ በእውቀት በሀሳብና በሙያ ዕድሜውን በሙሉ ሲረዳ ኖሮአል፡- በግል ገንዘብ ካቋቋማቸውና በኢትዮጵያ ካሰራቸው ቤተክርስቲያኖች ጀምሮ በግል ኑሮአቸውም የብዙ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል፡፡