በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እስር ላይ ያሉት የቀድሞው የሜቴክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው ኢሳይያስ ዳኘው፣ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ የደህንነት አቶ ተስፋየ ኡርጌ በዛሬው ዕለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
በዛሬው ፍርድ ቤት ውሎም ሌላኛው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የቀረቡት አቶ አለም ፍፁም ሲሆኑ ሪቬራ ሆቴልን ዋጋውን ከፍ አድርጎ ለሜቴክ በመሸጥም ፖሊስ ክስ አቅርቦባቸዋል።
የፖሊስ ክስ እንደሚያሳየውም ክፍት ባልሆነ ጨረታ ያላቸውን ግንኙነት ያላግባብ በመጠቀም ሆቴሉ ሊያወጣው ከሚችለው በላይ በ67 ሚሊዮን ብር ሸጠዋል ይላል።
አምስት ግለሰቦች በምስክርነትና፤ በተጠርጣሪውና በሜቴክ መካከል የነበረ ቃለጉባኤን እንደ ተጨማሪ መረጃነት ፖሊስ አቅርቧል።
ፖሊስ ለተጨማሪ ምርምራ 14 ቀነ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፤ተጠርጣሪው መረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ እንዲሁም ከሐገር ውጭ ሊወጡ ይችላሉ በሚልም የዋስ መብታቸው እንዲከለከሉ ጠይቋል።
አቶ አለም በቦሌ አካባቢ በግንባታ ላይ ያለ ባለ አራት ኮከብ ባለቤት ሲሆኑ ጠበቃቸውም የንግድ ሰው በመሆናቸውም ሊያዋጣቸው በሚችል መሸጥና መግዛት ይችላሉ በሚል ተከራክረዋል።
ጠበቃቸው በተጨማሪ ፖሊስ እንደመረጃነት ያቀረበው ሰነዶች ከመሆናቸው አንፃር ተጨማሪ አስራ አራት ቀነ ቀጠሮ እንደማያስፈልግ ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የአቶ አለምን ዋስ መብታቸውን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ይዟል።
በሌላ በኩል 14 ሚሊዮን ብር በህገወጥ መንገድ ከባንክ ሊያወጡ ነበር በሚል ፖሊስ የጠረጠራቸው አቶ ገመቹ ጫላ ላይ ፖሊስ ያለውን መረጃ አጠናቆ ነገ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ትዕዛዝ ፍርድ ቤት አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ የሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው ኢሳይያስ ዳኘው ጉዳይን ለመመልከት ጊዜ ባለመኖሩ ለረቡዕ ህዳር 26 ቀጠሮ ይዟል።
በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ አዲስ የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች ቀርበውባቸዋል።
አቶ ተስፋየ ፖሊስ ላቀረበባቸው ክስ ምላሽ ለመስጠት ፍርድ ቤቱን የሁለት ቀናት ቀጠሮ በጠየቁት መሰረት ለረቡዕ ህዳር 26 ምላሻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ
The post ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ለረቡዕ ተቀጠሩ appeared first on Bawza NewsPaper.