ራስህን አስተዋውቀን — ጥጋቡ ቸርነት ወይም መሃመድ —- እባላለሁ፡፡ ጥጋቡ የቤት ስምህ ነው? ዋ! ቤተሰቦቼ እኮ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ አያቴ መሃመድ ነበር የሚለኝ፡፡ ያው እኔ ተጠምቄ ነው፡፡ አንዳንዶች አሽቃባጭ፣ ፋረኛው ራፐር፣ ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ራሴን የምጠራው ‹‹አዳማቂው›› በሚል ነው፡፡ በፆም ወቅት ስንት ስራዎች ሰራህ?
አሁን ድምፃውያን ሙሉ ስራ ላይ ብዙም ትኩረት እየሰጡ አይደለም፡፡ ሞያተኛውም ሰርቶ ጥቅም ባለማግኘቱ፣ የኮፒራይቱም ጥሰት ተጠናክሮ በመቀጠሉ ወደ ነጠላ ዜማና ክሊፖች ነው አርቲስቱ እያዘነበለ ያለው፡፡ ወደ አስር ነጠላ ዜማዎች ላይ ተሳትፌአለሁ። የታዋቂዎችና የጀማሪ ባህላዊ ዘፈኖች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ለፋሲካ ባህል የሚወጡ ነጠላ ስራዎች አሉ፡፡ እንዴት ነው ሥራውን የጀመርከው፣ አርአያ የሆነህ ባለሙያ አለ? እገሌ የምለው የለኝም፡፡ ፈር ቀዳጅ አዳማቂ—- ፈር ቀዳጅ አሽቃባጪ በይው!! ..በገጠር ነው እድገቴ፡፡ በሀገራች ሁሉ አቀንቃኝ፣ ሁሉ ጨዋታ አዋቂ፣ ነገር አዋቂ፣..እንደመሆኑ በሰርግም ሆነ በጥምቀት አንዱ ግጥም ሲሰጥ፤ አንዱ ሲቀበል…ሌላው ሲፎክር፣ ሲሸልል…የውስጡን ስሜት በተረትና በምሳሌ ይገልፃል የባላገር ህይወት ይሄው ነው፡፡ በጋራ ሸንተረሩና በየመንገዱ ላይ .. ማንጎራጎር የተለመደ ነው፡፡ ቆይ ቆይ እንደውም አስተውለሽ እንደሁ — እዚህ አገር እኮ ይመጡልሻል—- ከገጠር አካባቢ —‹‹ሸበላው›› የሚባሉትን እስኪ ጠጋ ብለሽ ስሚያቸው—- ትርጉም የሌለው ዝም ብሎ ብቻ እንደሙዚቃ መሳሪያ ሲሉት…የድምፃቸው ማማር፡፡
/በድምፁ እያንቆረቆረ/ ገጠር የት ነው የተወለድከው፣ ያደከው? የተወለድኩት ጎንደር ነው፡፡ ያደግሁት ግን ባህርዳር። ጎንደር እፍራዝ ደንቢያ ፍርቃ ይባላል፡፡ ….. እናልሽ—–ገና ህፃን ሳለሁ —— ወላጆቼን በሽታ ጨረሳቸው፡፡ በወቅቱ በሽታ ገብቶ ነበር፡፡ በሰዓቱ ብዙ ከብትና ሰው አለቀ፡፡ ስምንት የወንድ አያቴ ልጆች ሞቱ፣ እናቴም ሞተች፣ የእናቴ እናት ሞተች…የተወሰኑ ሰዎች ስንቀር “አያቴ እነዚህን ላትርፍ፣ ዘሬን ላጣ ነው፣ እኔም ብሞት አጉል ነው” ብሎ የተወሰኑትን ቤተዘመዱን ይዞ ባህርዳር ገባነ፡፡ ባህርዳር ነው ያደኩት፡፡ አያቴ ነው ያሳደገኝ፡፡ አንተ ያን ጊዜ ስንት ዓመትህ ነበር? ወደ ሰባት ብሆን ነው፡፡ ብዙም ትዝ አይለኝ፡፡ የተወለድክበት ገጠር፤ ትዝታው የለማ? የተረፈው ዘመድ ተርፎ አሁን አሁን ሰርግ ይጠሩኛል እሄዳሁ፡፡ አንዳንድ የሩቅ ዘመዶችም ቢሆኑ አይጠፉም፡፡ ዋ!! መቼም አልተለየሁም ከገጠር፡፡ ሰርግ ላይ ተጠርተህ ስትሄድ ታቀነቅን ነበር ታዲያ? ዋ..ማ ብሎኝ—አስነካው፡፡ ‹‹እረ ፈሪ ብልጡ፣ እረ ጃርቲ ብልጡ ሲሮጥ የሚያይበት፣ አይን አለው በቂጡ ነፋስ ዶቄት ሰርቆ አይበላው አንጉቶ(2) ወደልሽ ሰደበኝ የአንቺን ነገር ሰምቶ…›› እያልን ለማማለል ..በሰርግ በዚያው የራስንም ለማግኘት..ጥቅሻው ይደራል፤ በግጥም መነቋቆሩ ይኖራል…በዚህ ጊዜ ‹‹አይ ድምፅ፣ አይ እስክስታው፣ አይ አንገቱ..›› ይባላል፡፡
የገጠር ሰርግ በከበሮ፣ በጡሩንባ፣ አጀቡ ሌላ ነው.—- አሁን “በሙሉ ባንድ ሙዚቃ ሰራን” ከሚባለው ኪነት እንኳን ድምቀቱ ሌላ እኮ ነው!! ተቀባዩ ብትይ፤ አድማቂው ሌላ እኮ ነው፡፡ ከዛ ፊት ግን ባህርዳር በልጅነቴ ገብቼ በእርሻው በከብት ጥበቃ ስራ ተሰማርቼ ባላየውም፣ የእኔ መኖሪያ ከከተማ ወጣ ይል ስለነበር አባይን ተሻግረን ‹‹ማክሰኝት..ዘንዘልማ›› የሚባል ቦታ እንሄድ ነበር፣ ከእኩዮቼ ጋር እንውል የነበረው ከአራዊትና ከእንስሳቱ ጋር በድር ነው። ልብሳችንን እናወልቅና ጭንቅላታችን ላይ ጠመጥመን..አባይን በዋና አቋርጠን ዶቅማ፣ ሾላ፣ እንኮይ፣ እሸ…” የተባሉ ፍራፍሬዎችን …እንለቅማለን፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ስንጫወት እናመሻለን፡፡ ጠላቂ፣ ዋናተኛ ነህ? ስሚ አባይን እኮ በዋና አቋረጥሽ ማለት ሌላ ሳይንስ ነው፡፡ ውሃው ሲወርድ እኮ እንዴት እንደሚማታ ..ብዙ ሰዎችን ያሳስታል፡፡ አልፎ ስታይው ድንጋይ ነው የሚመስልሽ፡፡ እና ሰዎች የአባይን ባህሪ ስለማያውቁት ቅርብ እየመስላቸው ስንቱን ውሃ በላው መሰለሽ። አንድ ቦታ የሚወርድ ይመስልሽና በደለል የተሸፈነ ወይንም በድንጋይ ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ ከጭንቅላቴ የማይወጣ እስከዛሬም ሳስበው ድርጊቱ ዝግንን የሚለኝ ነገር ገጥሞኛል።
በደርግ እና በኢህአዴግ ጦርነት ጊዜ የደርግ ሰራዊት በአባይ ተበልቷል፡፡ ጦርነቱ ሲገፋ ከኢህአዴግ ሰራዊት ለማምለጥ ብለው ሊሻገሩ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ጠርጎ ሲወስዳቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ዋናማ ለገጠር ልጅ ምኑ ነው፡፡ ያውም በአባይ ወንዝ ዋናን የለመደ፡፡ እኛማ ዝም ብለን አይደል ጠልቀን እምንሄድበት፡፡ አባይን ተሻግረን ቤዛዊት የሚባል የአፄ ሃይለስላሌ ቤተመንግስት አካባቢ በዋና እንወጣና በዱር በገደሉ ከዝንጀሮዎችና ከአራዊቱ ጋር እናመሻለን፡፡ ከዝንጀሮ ጋር ግብ ግብ ገጥመን ነው ያልኩሽን ፍራፍሬ የምንመገብ፡፡ እንደ ዝንጀሮ ተንኮለኛ የለም፣ ዝንጀሮን “አንዳንድ ተንኮለኛን ሰው ይመስላል” ሲሉ እሰማ ነበር፡፡ ዝንጀሮው ፍራፍሬውን ስንለቅም ተራራ ላይ ሆኖ ድንጋይ ይወረውርብናል፡፡ ከተራራ ላይ ሆኖ የድንጋይ ናዳ ይለቅብናል፡፡ አንድ ጓደኛዬ ዝንጀሮ ፈንክቶታል፡፡ እኛ ግን እንደ ጨዋታም ስለምናየው ከዝንጀሮው ዱላ ይልቅ እናቀነቅናለን…ድምፃችን ከገደል ገደል እየተላተመ፤ ከተራራ ተራራ እየተጋጨ የሚያሰማን የገደል ማሚቱ አይነት ነገር የራሳችንን ድምፅ እንድናውቀው፣ እንድንወደው ይረዳናል፡፡ ደጋገምን እንጮሃለን፣ እንዘፍናለን…ተፈጥሮ በራስዋ ከእኛ ጋር ስታውካካ ታመሻለች፡፡ ዋ!! ያልሽ እንደሆነ እኮ ደግሞ አንዱ ግጥም ሲሰጥ፣ አንዱ ሲቀበል ሲፎከር ሲሸለል ሳናውቀው ቀኑ መሽቶ ይነጋል፡፡ አመሻሻችንን ደግሞ በዋና ተመልሰን ወደ ሰፈራችን እገባለን፡፡
ዛሬ ፅፌ እንኳን ሙዚቃ አልይዝም፣ ያን ጊዜ ግን ምኑን ልንገርሽ፡፡ ቴፕ እንኳን በቤታችን ስለሌለ አዲስ ካሴት የምንሰማው ሙዚቃ ቤት ደጅ ላይ ቆመን ነበር። አንድ ሙሉ ካሴት ጀምሮ እስኪያልቅ…አንዳንድ ጊዜም የሙዚቃ ቤት በር ላይ እንደቆምን፣ አንድ ካሴት ብቻ እየተገለባበጠ እየሰማን ይመሻል፡፡ ሙዚቃ ቤቶችም እንደማሻሻጫ ሰው ሰምቶና አይቶ እንዲገዛቸው ስለሚፈልጉ ነው መሰለኝ…. እንደ ጉንዳን ሱቁን ከበን በምሳጤ ስናዳምጥ፤ አንዳች አይናገሩንም…ጭራሽ ካሴቱን እየገለባበጡ ያስደምጡናል፡፡ .. ማድመጥ ብቻ ነው ወይንስ ያደመጥከውን የባህል ምሽት ቤቶች እየዞርክ ታንጎራጉራለህ? ያን ጊዜ የምሽት ክበብ ብዙም አይታወቅም፡፡ እኔንም እዛ የሚያደርሰኝም የለ፡፡ ልጅ ነኝ!! በየጠላ ቤቱ እየተዘዋዟርኩ ሳቀነቅን፤ ስሸለም ነው የምውለው፡፡ ሰው ልብስ አጠባ ወንዝ ይወርዳል፤ ሲወርድ እኔም ወንዝ ወርጄ ስዘፍን ይሸልሙኛል፡፡ የትምህርትህስ ነገር —– መማር እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ ግን ድህነቱም ስለነበረ ቀን ቀን ሊስትሮ እየሰራሁ ምሽት ወደ ጠላ ቤት እየሄድኩ በግጥምና በማቀንቀን ጠጪውን ሳዝናና፣ በየሙዚቃ ቤቱ የሰማሁትን የነጥላሁን ገሠሠን ዘፈን ሳንጎራጉር — አልኩሽ ሽልማቱ ይዥጎደጉድልኝ ጀመር፡፡
ጠላም ያልሽ እንደሆን ያን ጊዜ ርካሽ ነው፣ አንዱ ማንቆርቆሪያ 25 ሳንቲም ነበር፡፡ ገንዘቡ እየተጠራቀመ ሲመጣ — መቶና ከዚያም በላይ በቀን ሳገኝ ..ደርሼ እያማረብኝ መጣ፡፡ አንድ ቀን ግን እዚያው የምሽት ክበብ/የምሰራበት ጠላ ቤት/ ውስጥ አንድ እክል ገጠመኝ፡፡ ምን ገጠመህ? ያን ግዜ ደረስን ደረስን የሚሉ ቡጢኛዎች ከምኖርበት ከከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው ሰፈሬ አካባቢ የሚገኙ ልጆች ያዙኝና ከዛሬ ጀምሮ እኛ በምንሄድበት ትሄዳለህ፤ የምንልህን ትፈፅማለህ፡፡ ከአሁን በኋላ በየጠላ ቤቱ እየሄድክ ብትዘፍን ውርድ ከራሳችን አሉኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ስላቸው ‹‹በቃ ጠላ ቤትም ቢሆን ከእኛ ጋር እንጂ ዝም ብሎ መንከውከው አይቻልም›› አሉኝ፡፡ ክብደት ያነሳሉ፣ ደረታቸውን ውጥርጥር አድርገው ሲጓዙ በጣም ያስፈራሉ፡፡ ቢደበድቡኝስ ብዬ ቀን ቀን ሊስትሮዬን እየሰራሁ፤ ማታ ማታ ከእነሱ ጋር በየጠላ ቤቱ እዞር ነበር፡፡ እነሱ ካልከፈቱኝና ከልዘጉኝ በስተቀር እኔ አንዳች መተንፈስ አልችልም ነበር፡፡ ማለት? ጠላ እየጠጣን የጠላ ቤት ታዳሚው ከዚህ ፊት እዘፍን እንደነበረ የሚያውቀው ሁሉ እኔን ሲያይ፤ ግብጦውን እና ቦቀልቱን ከጠላ ጋር እያሻመደ.. እሱ ምን አለበት… ‹‹አንተ ምነ ዛሬ ልሳንህ ተዘጋ፡፡ በል እንጂ አቀንቅን›› ይሉኛል፡፡ ልሳኔን በቡጢኞች ሊያዘጋ ስለሚችል ቃል አልተነፍስም፡፡ ከቡጢኞች መካከል አንዱ ተንስቶ ‹‹እራ….እኛ ሳንከፍተው ሳንዘጋው አያቀነቅንም›› ይላል፡፡ በኋላ እንደ ቡጢኞች መልካም ፈቃድ ትከሻዬን በአውራጣቱ ጫን ብሎ ‹‹ቀጭ›› ይለኛል፡፡ በእርሱ ቤት ቴፕ እንደመክፈትና እንደ መዝጋት ነው፡፡
ያን ጊዜ መዝፈን እጀምራለሁ፡፡ እንደገና ‹‹ቀጭ›› ሲለኝ ስዘፍን የነበርኩት አቋርጣለሁ፡፡ ጠላ ቤት ይዘውኝ የሚሄዱት 25 ሳንቲም፣ 50 ሳንቲም ሲያገኙ ነው፡፡ ያም ሳንቲም ሆኖ የሚጠፋበት ጊዜ ነበርና አንዳንድ ጊዜ ወንዝ ይዘውኝ ይወርዳሉ፡፡ እነሱ እየታጠቡ ..እነሱን እኔ አዝናናለሁ፡፡…ወንዝ ይዘውኝ ወርደውማ..ቴፕን እስከ መጨረሻው እንደመክፈት ቁጠሪው‹‹…ድምፅህን ጎላ አርገህ ዝፈን…አትሰማም…ቀይር…አቅጥን …አወፍር…›› ሲሉኝ — ስዘፍን አንዱን ስል አንዱን ስጥል እውላለሁ፡፡ ስራም አልሰራሁ፣ እነሱ ወደ ቤታችው ሲሄዱ እኔ የምበላውም አይኖረኝ፣ አንጀቴን አጥፌ እውላለሁ፡፡ በጣም መቸገር ጀመርኩ፡፡ ‹‹የፈለገው ይምጣ›› ብዬ ጠፍቻቸው ሊስትሮዬን መስራት ጀመርኩ፤ የመንግስት ሰራተኞች ከቤታቸው መስሪያ ቤታቸው ምሳቸውን አደርሳለሁ — በዚህ በዚህ ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩ፡፡ አንዱ ቀን ከእነሱ ጋር ጠላ ቤት ሂጄ ‹‹ለምን ገንዘብ አዋጥተን ልብስ አንገዛለትም›› ብለው ጠላ ቤት ውስጥ የብር መሰብሰቢያ ሰሃን አስቀምጠው፣ የጠላ ቤቱ ሰው ሁሉ አዋጥቶ በወቅቱ ፋሽን የነበረ እንዴት ያለ ማራዶና ቱታ ከአዲዳስ ጫማ ጋር ገዙልኝ፡፡
አቤት ከእኔ በላይ ሰውም ያለ አልመስል አለኝ፡፡ እዚያው ጠላ ቤት ነው እድሌ የወጣች ..አንዱ ቀን እዚያው ጠላ ቤት ስዘፍን የ‹‹ባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ/ኮተኒ›› ይባላል፤ የዛ መስሪያ ቤት ሰራተኛ የሆኑ ሰዎች አለቆች አገኙኝ ፣ በወቅቱ ፋብሪካው ኪነት ነበረው፡፡ ሙዚቀኛ ይፈልጉ ነበር፡፡ ሲያዩኝ ‹‹አንተ እንደዚህ በየጠላ ቤቱ እየዘፈንክ ዝናህን ሰምተን ነበር..እንዴት ያለኸው ልጅ›› አሉና ይዘውኝ ሄዱ..በፋብሪካው ለነበረው የኪነት ቡድን በወጣ ማስታወቂያ ከተወዳደሩ ሁለት መቶ ሰዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ተቀጠርኩ፡፡ በስንት ብር ደሞወዝ? ደሞዝ? ከቴም ደሞዝ!! እረ የለውም፡፡ የኪስ ገንዘብ ነው፤ 50 ብር፡፡ ጠላ ቤት በቀን የምታገኘው አይበልጥም—- በ50 ብር ከምትቀጠር? እሱማ ነው ግን— የመንግስት ስራ ነው፡፡ ከቀን ቀን ይሻሻል ብዬ በማሰብ እንጂ ምን አከላት አለው ብለሽ ነው 50 ብር፡፡ በ50 ብር ስንት ዓመት ሰራህ? አራት ዓመት ሰራሁ፡፡
ግን ከሸክም እስከ ሊስትሮ ብቻ ህይወት እንድትቀጥል የሚያስችላትን የትኛውምን ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ እሰራ ነበር፡፡ ከዚያ እዚያው ባህርዳር ጊሽ ዓባይ ኪነት ማስታወቂያ አወጣ- ተወዳድሬ አለፍኩ፡፡ በድምፃዊነት ነው? በድምፃዊነት ነበር ያለፍኩት ግን ‹‹ሁለገብ መሆን ያስፈልግሃል›› ተብዬ ወደ ውዝዋዜውም ገባሁ፡፡ በመቶ ሃያ ሰባት ብር ነበር የተቀጠርኩት፡፡ እነ ሰማኸኝ በለውን፣ ይሁኔ በላይን፣ ስፈልግ አያሌውን፣ እነ ወይኒቷን ያፈራ ኪነት ነው፡፡ ጊሽ ዓባይ ኪነት ወደ አራት ዓመት ሰራሁ — ግን እሱም ወዲያው ኢህአዴግ ገባና ኪነቱም ተበተነ፡፡ በጊሽ ዓባይ ኪነት በነበረህ ቆይታ ጦሩን ለመቀስቀስም ወደ ጦር ግንባር ከቡድኑ ጋር የመውጣት እድል አግኝተህ ታውቅለህ? አንዱ ጊዜ ወደ አስመራ ጦሩን ለመቀስቀስ ሲኬድ የመሄድ እድል ገጥሞኝ ነበር፣ ነገር ግን ተመካክረው ቀነሱኝ፡፡
‹‹ልጅ ነው— በረሃ ውሃ ጥም አይችልም›› ብለው፡፡ ከዚያስ የአንተ እጣ ፋንታ ምን ሆነ? ኢህአዴግ ሲገባና ደርግ ሲበተን፣ ጊሽ ዓባይ ኪነት የመበተን ዕጣ ገጠመው፣ ስለዚህ የቡድኑ ዕቃ ነበር ተሸጦ ገንዘቡን ተከፋፈልነው፡፡ ሰው ሁሉ ይመክረኝ ጀመር። ‹‹እዚህ አገር ከሆንክ የማንም ጠላ ጠጪ አጫዋችና አጋፋሪ ሆነህ ነው የምትቀር እና ወደ መሃል አገር ሂድ›› አሉኝ፡፡ ስንከፋፈል የደረሰኝ 2ሺህ ብር ይዤ ‹‹አይን አፋር ሲሄድ አያፍር›› በሚባለው በሽንጣሙ አውቶብስ ተሰቅዬ —በአይናፋሩ ስከንፍ አዲስ አበባ መጣሁልሽ፡፡ ዘመድ ነበረህ — አዲስ አበባ? እኔ ነው?! እራ እንዴት ያለሽው ነሽ—- ከየት አምጥቼው፡፡ የአዲስ አበባ ዘመድ ደግሞ ሰው ሲመጣበት አይወድም፡፡ ገና ‹‹ሰላም መጣሽ›› ከማለቱ ‹‹መቼ ልትሄድ ነው የመጣኸው›› ነው የሚልሽ፡፡ ቤት ኪራይ ኑሮው እየመረረው ነው መሰል..፡፡ እብዛም ደግሞ ዘመድ የለኝም፡፡ የት አረፍክ ታዲያ? እራ እንደመጣሁ እማ.. ምን መሄጃ አለኝ፡፡ ያረፍኩት ጎጃም በረዳ አካባቢ ካለ ሆቴል ነው፡፡ በቀን ስምንት ብር እየከፈልኩኝ፡፡ ውድ ነው፡፡ ግን ስልክ ቁጥር ይዤ መጥቼ ነበር፡፡
ያን ጊዜ እነ ሰማኸኝ በለው፣ ይሁኔ በላይ፣ እነ አንሙቴ..የጊሽ ዓባይ ልጆች በሙሉ ወዲህ ዘልቀው ነበር። ብቻ ግን ‹‹..የሆነው ይሁን›› ብዬ ነው የመጣሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ፤ አንድ ነገር አስጠነቀቁኝ፡፡ ‹‹ዘንጦ፣ ሸልሎ፣ ሽክ ብሎ፣ ሱፉን ከረባቱን አድርጎ የምታየው ሰው ሁል ጤነኛ እንዳይመስልህ ሌባ ነው›› አሉኝ፡፡ ከአልቤርጎ እንዳልወጣ ሰፊ ነው ሃገሩ፡፡ ‹‹ብጠፋስ›› ብዬ የምውለው የምበላው እዚያው መኝታዬ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ቀን ከአልቤርጎው አጠገብ ካሉ ሊስትሮዎች ጫማ እያስጠረኩ …የመኪና መለዋወጫ ስፔር ፓርት አለ፣ እሱ አጠገብ አንድ ሰው ቆሞ በአመክሮ ያየኛል፡፡ እንዴት ያለ የሸለለ መሰለሽ፡፡ እንዳ አጋጣሚ አቀርቅሬ ቀና ስል፤ አይን ለአይን እንገጣጠማለን፡፡ ቆየት ብዬ ቀና ስል፤ አሁንም አይን ለአይን እንገጣጠማለን፡፡ ‹‹አይ ሌቦ…ዋ!! እንዴት አድርጎ ነው የሚያየኝ፣ ሆዱን ለቅቶ›› .. በውስጤ እጫወታለሁ፡፡ ሲልስ ማጉረጥረጡን ያበዛብኝ መሰለኝ፡፡
ተነሳሁና በስድብ አጥረግርጌ ‹‹አንተ ሞሽላቃ ሌባ…የእንጨት ሽበት፣ አሁን ይሄን ሽበት ይዘህ..አሁን ይሄን ሽበት ይዘህ ትሰርቅ…›› አልኩት። እንደ ምንሜና ለወጠኝ፡፡ ሰውዬው እንደ መደንገጥ አለ። ሰው ተሰበሰበ.. ‹‹ምን ሆነህ ነው፤ ምን ሆነህ ነው›› እያሉ ጠየቁኝ፡፡ ‹‹ዋ አፍጦ እያየኝ..ምን ይሄማ አላወቃችሁትም እንጂ ሌባ እኮ ነው›› እያኩ እደነፋልሻለሁ፡፡ ሰው መደናገሬ ስለገባው ‹‹እረ እሻ…እረ እሻ..ሰውዬው የቆምክበት የስፔር ፓርቱ ባለቤት ነው›› ብለው ሲሉኝ ወከክ ብዬ ቀረሁልሽ፡፡ ዱላ ቀመስካ— እረ!! ባለማዋቄ ተገርመው፣ አዝነው እንዴውም..ተሳስቀው ዝም አሉኝ፡፡ አንድ ቀን እዚያ ጎጃም በረንዳ የኪነት ጓዴን አንሙቴን አገኘሁትና አወጋን፡፡ በቃ እኔ ቤት ልከራይልህ ብሎ ካሳንቺስ ይዞኝ መጣ፣ ወይ አገር …አዲስ አበባን እያደነቅሁ የከተማ ልጅ ሆንኩኝ፡፡ ስወጣ ስገባ አካባቢውን እየለመድኩት መጣሁ፡፡ ካሳንቺስ አካባቢ ያሉ የምሽት ክበቦች ማምሻዬን መዞር ጀመርኩ። ምሽት ቤቶች በር ላይ ቆሜ ሲዘፍኑ እሰማለሁ፡፡ ወደ ውስጥ አልገባም፡፡ ካሳንቺስ ዮርዳኖስ ሆቴል ፊት ለፊት ጥሩ ምግብ ቤት የሚባል ቤት ነበር፡፡
እሳቸው ቤት ሄድኩ..ዘበኛውን አስገባኝ ስለው፣ ‹‹ምን ታደርግ?››አለኝ ‹‹ከጎጃም ነው የመጣሁ፣ ባለቤቲትን ማግኘት እፈልጋለሁ፡፡ ዘፋኝ ነኝ ›› ስለው ‹‹በል መልካም ሰው ናቸው— ግባ እና አናግራቸው›› አለኝ፡፡ ሳናግራቸው “በል እስቲ ከዘፋኞች ላገናኝህ” ብለው አገናኙኝ፡፡ ዘፋኞቹ ‹‹እስቲ ሞክር›› ብለው ሲሉኝ ሳቀነቅን.. “ዓይነተኛው መጣ” ብለው ደስ አላቸው፣ ያንን ምሽት በምሽት ክበቡ ስዘፍን አመሸሁ— ሽልማቱ ሌላ ነበር፡፡ የራስህ ዘፈን ነበር? ‹‹አንቱየዋ›› የሚለው የይሁኔ በላይን ነው፡፡ እራ እነዛ ‹‹ሞክር ዝፈን እስቲ›› ያሉኝ እኮ እያላገጡ ነበር። በደንብ እምሰራው አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ሽልማቱ ቢዥጎደጎድልኝ ‹‹እረ እንዴት ነሽ ገንዘብ›› አልኩኝ፡፡ ገንዘቤን ተቀብዬ እግዚአብሄር ይስጥልኝ ብዬ ወጣሁ። በቤት ኪራይ ተወጥሬ ተይዤ ነበር…አከራዮቼን ባየሁ ቆጥር ነፍሴ ድርቅ እያለች ነበር፡፡ ሽልማቴን አግኝቼ ስመለስ ቀድሜ የአራት ወር የቤት ኪራይ ሁለት መቶ ብር ከፍያቸው ተገላገልኩ፡፡ ጥሩ ምግብ ቤት ተቀጠርክ? ወይስ— እረ የለም፡፡ በቂ ሰው ነበራቸው፡፡ ይልቅስ ከጥሩ ምግብ ቤት አጠገብ ይሁኔ በላይና ሰማኸኝ በለው የሚጫወቱበት የምሽት ክበብ ነበር – ‹የሽዋ ጌጥ› የሚባል ..እነሱ በሃገር ባይኖሩም፡፡
ቦታውን ማወቄ አገር እንዳወቅሁ —ደስ እያለኝ መጣ፡፡ ስል ስል እየለመድኩ በባህል ዘፈን ታዋቂ የሆኑ እነ አሸብር በላይ፣ ፋሲል ደሞወዝ፣ ጌቴ አንለይ …በሚሰሩበት የምሽት ክበብ ሌላ ስራ ሲኖራቸው እኔ የሚሰሩበት ቦታ እየተገኘሁ የእነሱን ቦታ መሸፈን…ጀመርኩ፡፡ በየትኛው የምሽት ክበብ ነው? ‹‹ከተፋ ቤት›› ይባላል፡፡ ድስትም ምጣድም አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት በማባለቻ እንደሚሟሸው እኔም ራሴን በምሽት ክበቦች እያሟሸሁ ቆየሁ፡፡ እነሱ በሚሰሩበት ቦታ እየሄድኩ የነሱን ስራ ሽፈና ማለት ነው፡፡ የራስህን ካሴት አላወጣህም? አይ እናት አለም…አንድ ሞክሬ ነበር፤ ሳይሳካ ቀረ። አልተሸጠም፡፡ በአዲስ አበባ የባህል ምሽት ክበቦች እየተገኘሁ የባህል ዘፋኞችን ስራ ሽፈና ቀጠልኩ፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ከባህል ዘፈኖች መሃል እየተሰነቀርኩ ራፕ ማድረግ…ማሽቃበጥ በይው—- እሰራለሁ፡፡ የከተማ ሰዎች ‹‹ራፕ የሚያደርገው—አሽቃባጩ– ፋርኛው ራፐር›› ይሉኛል፡፡ የገጠሩ አድማጭ ደግሞ ‹‹አዳማቂው›› መጣ ይላል፡፡ አድማቂ ቢባል ይሻላል፡፡ አሽቃባጩ ማለት እኮ..አድርባይ አይነት ይሆናል..ሞያ ነው— የህዝብ ባህል ነው፣ ማክበር እፈልጋለሁ፡፡ በአዳማቂነት ለመጀመርያ ጊዜ በካሴት የሰራኸው ከማን ጋር ነው? በማናልቦሽ ዲቦ ዘፈን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራሁት፡፡ ስቱዲዮ ተጠርቼ ተቀረፅኩኝ ‹‹ሆይ መላ ነሽ አሉ ሆይ መላ›› ብላ ስትዘፍን እኔ ‹‹አለው መላ መላ›› ብዬ ሙዚቃውን ልቀበል ነበር የሄድኩት፡፡
ስቱዲዮ ውስጥ ገብቼ ኤርፎኑን ጆሮዬ ላይ ካደረኩኝ በኋላ ….አንድ ሃሳብ መጣልኝ… ‹‹ጠላው ተደርጎ፣ ቡናው ተፈልቶ፣ ዘመድ ተጠራርቶ፣ እንዲያ ነው ዓመት በዓል›› እያልኩ ስጨማምር…በጣም ወደዱት፡፡ በዚያው ይሄው ከሁለት መቶ በላይ ዘፈኖች ላይ ከታዋቂዎች እስከ ጀማሪዎች የባህል ዘፋኞች አድማቂ ለመሆን ቻልኩ፡፡ ከዛ በኋላማ ለቁጥር በሚያታክቱ የጎጃም፣ ጎንደር፣ወሎ ..እነ አቤል ሙሉጌታ፣ ማዲንጎና ብሩሃኑ ተዘራ “አንበሳው አገሳ”— ገነት ማስረሻ፣ ግዛቸው፣ ብርቱካን ዱባለ — ምን ልበልሽ…. ዘመናዊውን አልነካሁም እንጂ— በባህል ዘፈን ላይ ግን አድማቂው— የባህል ሙዚቃ ራፐሩ እኔ ነኝ፡፡ ልዩ ትምህርት ወይም ተሰጥኦ ይጠይቃል? እራ.. በገጠር የባህል ዘፈን ውስጥ እኮ ያለ ነው። አንዱ ሲያቀነቅን — አንዱ ያዝ፣ ተቀበል፣ ውጣ፣ ውረድ፣ እንደዚህ አርገው፣ ወይ ጥጋብ፣ ወይ አመል፣ ያዝ፣ ተቀበል—- ሲል ነው የሚደመጥ፡፡ በጎጃም ብትይ በጎንደር..ከባንድ በላይ እኮ የሰርግ ዘፈን በገጠር ይደምቃል፡፡ በሰርግ፣ በጥምቀቱ እንዘፍናለን..ሰርግ ጥሪ ስንገኝ እየተበላ፣ እየተጠጣ፤ ፉከራ ነው፣ ማቀንቀን ነው—- ሌላ ነው አልኩሽ፡፡ እኔ ከሙዚቃ ጋር ቅኝቱና ንግግሩ እንደዜማ ሆኖ በሙዚቃው ውስጥ እንዲሆን ነው ያደረኩትኝ፡፡ ያ ነው ለየት የሚያደርገኝና ወደ ፈጠራ የሚያመጣኝ፡፡ ቃሎችን እራሴ ፈጥሬ፣ ዘፈን ሰምቼ — ዘፈንን የማቃናት ስራ ነው የምሰራው፡፡
ሙዚቃውንና ዘፈኑን እሰማለሁ እና ርዕሱን አያለሁ— ሊል የፈለገው ምንድን ነው የሚለውን አዳምጬ፣ ያልተቃናውን ማቃናት፤ ድብስብስ ያለውን ደግሞ የመግለፅ ስራ ነው የምሰራው፡፡ “እሰይ መጣልን አውዳመት ..እያለች” ስትዘፍን ማናልቦሽ ..እኔ ያሰብኩት “አውዳመት መሃል ምን አለ?” የሚለውን ነው፡፡ ዘመድ ይጠራራል፣ ጠላው፣ ቡናው፣ ዳቦው…ይሄንን ነው፡፡ ይሄው እንዳዳመቅሁ እንዳሽቃበጥኩ አለሁ፡፡ ግን መብያ አድርጎልኝ እግዚሃቤር.፡፡ አንድ በጣም የሚከፋኝ ነገር አለ፡፡ እንደዚህ ለባህሉ ሙዚቃ ማማር እየሰራሁ—- ለሞያው ክብር ያለመስጠት ይሁን ሌላ…በሙዚቃው ውስጥ ከካሜራ ማን እስከ…አልፎ ሂያጁ ድረስ ስምና ማንነት ሲጠቀስ — በክሊፕም ሆነ በካሴት “አድማቂ ጥጋቡ ቸርነት” ብለው ገልፀው አያውቁም፡፡ በአንድ ዘፈን ለአድማቂነት ስንት ይከፈልሃል? አይ እሱ ነው አበሳው…በነፃ ከመስራት ጀምሮ፣ እስከዛሬ ትልቁ ስድስት መቶ ብር ነው የተከፈለኝ፡፡ መተዳደሪያህ ይሄው ነው? ከማሽቃበጡ በተጨማሪ በሸዋጌጥ፣ በአይቤክስ፣ በሁለት ሺህ አበሻና በብዙ ናይት ክለቦች ውስጥ ሰርቻለሁ።
አሁን ደግሞ ደሳለች ክትፎ፣ ቦሌ ነው የምሰራው… ሰርጎች ላይ የተለያዩ የባህል ስራዎች እሰራለሁ፡፡ ያለ አንተ አዳማቂነት የተሰሩ ዘፈኖችን ሰምተህ እዚህ ቦታ ላይ እኔ ብኖር ኖሮ ያልክበት አጋጣሚ አለ? በጣም በርካታ እንጂ— ክፍተት ከመሙላት ጀምሮ እስከ ልዩነት ማምጣት ድረስ፡፡ አንዳንዴ አለመገጣጠም ይሆንና አያስቡትም፡፡ አንዳንዴ ለአንድ ዘፈን የተቀረፅኩትን ለሌሎች ድምፃውያን አስገብተውት አገኛለሁ፡፡ ይህችም እንጀራ ሁና!! እንደ ኮፒ ራይት ጥሰት አስቢው፡፡ መጥታ እንኳን ጉሮሮ የማታረጥብ…ይሄ በጣም እየረበሸኝ ነው፡፡ ለምን መሰለሽ በጣም እየተለመድኩ መጣሁ፡፡ በገጠር ‹‹እኛ ሽማግሌ የሌሉበት ሙዚቃስ አይደምቅም›› ይላሉ፡፡ ሸመገልክ እንዴ ጥጋቡ እስቲ ዕድሜዬን በአይተሽ ሙይው እንዳላሳንስብህ አንተ ንገረኝ እርግጡ 30 ዓመቴ ነው፡፡ ትዳር፣ ልጆች? ሶስት ልጆች አሉኝ፣ አግብቻለሁ፡፡
source: addis admas newsletter
The post Tigabu Cherenet: “Ethiopian traditional music rapper !” appeared first on Bawza NewsPaper.