Quantcast
Channel: Bawza
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

“ሹፌር አፍጥነው። ያን እንቦጭ ድረስበት!

$
0
0
አክስቴን ጥየቃ (ጓዴ ጥላሁን)
 
ዛሬ በጥዋቱ ከባህር ዳር ጥቂት ያህል ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን አክስቴን ለመጠየቅ ታክሲ ያዝኩ። ወዲያው አንድ ወመኔ መካኒክ ነኝ ባይ ታክሲያችን የማገት ያህል አስቁሞ ገባ። “ሹፌር አፍጥነው። ያን እንቦጭ ድረሰበት። ጀርባውን ነድዬው ልመለስ…” ሲል ይፎክር ጀመር። ተሳፋሪው በሙሉ ተደናግጠን ዝም አልን። እሱ ይዝታል። ከብዙ ዝምታ በኋላ ተናጋሪ ሲጠፋ “ይቅርታ ልናገር?” ስል ተማፀንኩት። እሱ አሁንም ይሸልላል። ትንሽ የታገሰ ሲመስለኝ ስፈራ ሥቸር “ማን ምን አርጎህ ይሆን?” አልሁት። ከረጅም ዝምታ በኋላ… “የንሰራበት ድረስ መጥቶ አንድ ሹፌር የቡለን መፍቻ ጠየቀኝ። ልተባበረው ብዬ ሰጠቸው ወደ ሥራዬ ዞርኩ። ስመለስ የለም። ሞጭልፎኝ ሂዷል። ይህን የሰው እንቦጭ ሳላነቡጨው ከቀረሁማ ያነቡጨኝ” በመሃል አንድ ተሳፋሪ “ወራጅ” አለ። ሜካኒኩ “ሹፌር እንዳታቆም። መጭ በለው። ወራጅ የሚልህ የሌባው ተባባሪ ነው” ብሎ አይኑን ሲያጉረጠርጥበት ወራጁ ድምፁን አጥፍቶ ጉዞውን አብሮን ቀጠለ። “ለመሆኑ የቡለኑ መፍቻ ውድ ነው?”ስል ጠየኩት። አዋጥተንም ቢሆን እንድንከፍለው በማሰብ። “ጥቃት አልወድም። ጥቃት ቢሆንብኝ ነው” “የሆነውስ ሆኖ ስንት ነው?” ” ነገርኩህኮ አትሰማም። ለታክሲ መሄጃና መመለሻ ከምከፍለው ቢያንስ እንጅ አይበዛም። ሹፌር ምናለበት ብታፈጥነው። ነው ወይስ አንተም የሌባው ጀሌ ነህ። እንዲያ ከሆነ ምስህን ልስጥህና ወደ ሥራዬ ለመለስ” ከምኔው ታክሲዋ ወደ ጀትነት እንደተቀየረች እሱ ይወቅ። ሹፌሩ 180km per hour ላይ አድርጎ ያግለበልባት ጀመር። እንደጉድ በረርን… መውረጃዬ ላይ የደርስሁ ቢሆንም ፍልሚያውን ለማየት ካለኝ ጉጉት ይሁን ወራጅ ያለው ሰውዬ እጣ ፈንታ እንዳይደርስብኝ ስለሰጋሁ የመውረጃ ፌርማታዬን አልፌ እከንፋለሁ። በመሃል ግን የሚያሰጋ ሀሳብ መጣብኝ። ሜካኒኩ ሌባውን ሹፌር ሳያገኘው ቢቀር በእርሱ ፈንታ እንደ ‘አንደር ቴከር’ አንድ ባንድ እያነሳ ወደ መሬት ቢደባልቀንስ … ሌባው ሹፌርስ ቢሆን ከዚህ ወጠምሻ እንኳን መስረቅ እንዲያውሰው መጠየቁስ ምን ያለው ደፋር ቢሆን ነው? ታክሲው እየሄደ እያለ በሩን በድንገት ከፍተህ ዘለህ አምልጥ አምልጥ አለኝ። ግን ሌባው መስየው በዛው ፍጥነት የሜዳ ፍየል ላይ እንደሚከመር ነብር ላዬ ላይ ቢከመርብኝስ? ይህማ አያዋጣም… እና ምን ተሻለ… የቸገረ ነገር… ሰውየው እንደሁ አንዴ ጠብ ፈልጓል። “ዛሬ ጠብ አምሮኛል ቢለው ‘የት ታገኛለህ?’ ያለውን ‘የታባህ አጣለሁ” ብሎ እንከደነበት ሰውዬ አንዳችን ላይ ሳይከድንብን አይቀርም። በዚህ መሃል ትራፊክ ፖሊስ ታክሲወን ፊሽካ በመንፋት አስቆማት። እኛን ለመታደግ የተላከ ቦርጫም መሆኑ እንጂ መልአክ ነው የመሰለኝ። “ከልክ በላይ ፍጥነት በማሻከርከር መንጃ ፍቃድ…” ሲለው እኔ ፈጥኜ በመውረድ እስከ አክስቴ ቤት ድረስ ሮጥሁ። ከአክስቴ ቤት በሩጫ እንደደረስኩ ውሻቸው ተቀብሎ እስከ ጉረቤት ቤት ድረስ አስሮጠኝ እላችኋለሁ!

 

The post “ሹፌር አፍጥነው። ያን እንቦጭ ድረስበት! appeared first on Bawza NewsPaper.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1835

Trending Articles