..ዘሪቱ እጅግ በራስ መተማመን ያላት ኢትዮጵያዊ ናት። የምታምንበትን ሳትፈራ መናገሯ ብዙ ጊዜ ለውዝግብ ሲዳርጋትና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲያስተቻት ቢቆይም ዛሬም በዲፕሎማሲ ቂቤ የተሟሸ አስመሳይ ምላስ የላትም። ልቧ ያመነበትን ትናገራለች እንጂ ሰው የሚፈልገውን ቃል ገጣጥማና ተለማምዳ አትቀባጥርም። በዚህ አስመሳይ የእከከኝ ልከክህ ዓለም ራስን ሆኖ መገኘት ከባድ ነው። የዘሪቱ የማንነት እምነት ከስሟ ይጀምራል። ስምን ማሞላቀቅና ምዕራባዊ ይዘት ባላቸው ቃላት ሾርት አርጎ ማቅረብ ስልጣኔና ከዘመኑ የመዛመድ እውቀት ሆኖ በሚታይበት በዚህ ዘመን ዘሪቱ በስሟ ላይ አርቴፊሻል ቃላት በዘረመል ማብቀል አልፈለገችም። ምናልባት በሀገራችን እየጠፉ ካሉ አበሻዊ የሴት ስሞች መካከል ዘሪቱ ከቀደሙት ተርታ የተሰለፈ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ዘሪቱን አብዛኛው ሰው ያወቃትና ይህቺ ደግሞ ከየት የመጣች ምትሃተኛ ድምፃዊ ናት? ያለው አልበም ከመስራቷ ቀደም ብሎ በተለቀቀ የHIV የማስተማሪያ ህብረ ዜማ ላይ ነበር። በወቅቱ ሙሉ ፀጉሯን ሙልጭ አድርጋ ተነስታ፣ ከላይ የሀዘን በሚመስል ጥቁር ጨርቅና ከታች ጠባብ ጅንስ ሱሪ አጥልቃ…..” መላ መላ መላ_ ወገን አትበል ችላ!” የሚለውን በርካታ አንጋፋ ድምፃዊያንን ባሳተፈው ዜማ ላይ በተሰጣት የሜሎዲ ድርሻ ሌሎቹ ድምፃዊያን አድማጭ እስኪመስል ለብቻዋ ፈንጥቃ የወጣች ከዋክብት ሆና ነበር። በዚህ ዘፈን ላይ ዝግ ብለው የሚጀምሩት ሌሎች ድምፃዊያን እየተቀባበሉ ይመጡና እጅግ ጉሮሮ የሚፈትነው የዜማው ስኬል ላይ ሲደርሱ የመጫወቻ ሜዳውን ለዘሪቱ ሲለቁላት…….” እንዴት በእንጉርጉሮ የተቃኘ ድምጿን ከረጅም የዜማ መዳረሻ አድማስ እንደምትለቀው ያደመጠ ሰው ሁሉ ይህቺ ልጅ እስከዛሬ የት ተደብቃ ኖራ ነው?” ብሎ መነጋገሩ አልቀረም። የዜማው አፅመ_አስኳል ኮንክሪቱ የታነፀው በእሷ ድምፅ ላይ ስለነበር የእሷን የዜማ ፓርት ቆርጠው ቢያወጡት፣ ዘፈኑ እንኳን HIV ለማስተማር ይቅርና ከማባባሻ መንገዶች አንዱ ይሆን ነበር ሲል የግነት አድናቆትን በወቅቱ የቸራትን ልጅ አረሳውም። አንድም የዘሪቱ ድምፅ ውስጡን በመደመም ያተራመሰው ልጅ “ኤች አይ ቪ መድሃኒቱ ተቀምሞ ይገኝ ከተባለ ምርምሩ መካሄድ ያለበት ላብራቶሪ ውስጥ ሳይሆን የዚህች ልጅ ጉሮሮ ውስጥ ነው! ያኔ በትክክል የእሷን ድምፅ ሲሰማ ኤድስ ከሰው ልጆች ላይ የጥፋት እጁን ያነሳል!!” በማለት የዘሪቱን አዲስ ታለንት እስከመድሃኒት አድርሶት ነበር።
…በእርግጥም ዘሪቱ ያልታሰበች የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ግኝት ኮከብ ነበረች። ብዙም ሳትቆይ በየቤቱ መገረምን የበተነችው ዘሪቱ ሙሉ አልበሟን በኤልያስ መልካ ስቱዲዮ መስራት ጀመረች። ታዲያ ስራው ከስቱዲዮ አልቆ ማስተሩን ገዝተው ገበያ ላይ ሊያውሉት ስራው የተመቻቸው ነጋዴዎች አንድ ነገር ቆረቆራቸው! ያም ዘሪቱ የሚለው ስሟ አልተመቻቸውም። የነጋዴዎቹ ፍርሃት የመነጨው ስራው ምርጥ ቢሆንም “ዘሪቱ” የሚለው ስም የድሮና ቅሪቱ ምናልባትም ያለው ከኋላ ቀር የገጠሪቱ መንደር ውስጥ ስለሆነ፣ ዘመናዊ ሙዚቃ ከሰራችው ዘመነኛ ሴት ጋር ማች አያደርግም፣ በዚያ ላይ በአልበሙ ገበያ ላይ አሉታዊ ተፅህኖ ይፈጥራል በሚል ነበር። ከራሳቸው የገበያ ጥቅም ተነስተው ማንነቷንና የምትኮራበት ስሟ ከመዝገብ ይፋቅና ፈረንጅኛ ቁልምጫ ይለጠፍልሽ ስትባል እንዴት ትስማቸው? ከፈለገ ሙዚቃው ጥንቅር ይበል እንጂ ስሜን ልቀይር ይቅርና አንዲት ፊደል አጥሮ ብጠራ እንኳን አልስማማም! አለቻቸው። አማራጭ ሲያጡ “እሺ ዜድ ይባል!” ብለዋትም ነበር። “ምንድነው ዜድ ማለት? ስም ነው? ስፔሊንግ? ለመሆኑ ምን ትርጉም ይሰጣል?” አለቻቸው። አቋሟን ሲያዩት ፍንክች የምትል አይነት አይደለችም። እሷ ግን “ስሜን መቀየር ይቅርና፣ የአልበሙ ርዕስ ራሱ ከአንዱ ዘፈን ላይ ተወስዶ ታይትል እንዲሆን አልፈልግም፣ አልበሙ አውራ መጠሪያው ራሱ “ዘሪቱ” መሆን አለበት!” ብላ ስሟን የት ድረስ እንደምትወደውና እንደምታከብረው አስረግጣ ነገረቻቸው። ዘሪቱ በሚለው ስምና ዘሪቱ በሚል መጠሪያ የወጣው ይኼው አልበም አድማጩ ስሟን ነገሬ ሳይለው ዳር እስከ ዳር ሰማላት። በአጭር ጊዜ በሕዝብ ልብ ቦታ ካገኙ ምርጥ የሀገራችን ድምፃዊያን ተርታ ለመሰለፍ በቃች። ስሟም እንደ አዲስ ጣፋጭ ሆነ፣ ዘሪቱ የሚል የማንኛውም ሰው ስም ሲጠራ ከሁሉም ፊት ድቅን የምትለው እሷ ሆነች። አንዲት አድናቂዋም የሴት ልጅ እናት ስትሆን መጠሪያዋን ዘሪቱ እንዳለቻት አስታውሳለው። መቼም ከዚህ በላይ በራስ መተማመን ምን አለ? የሰው ክብሩ ከራሱ ይጀምራል። ዘሪቱም የድሮ ስም፣ ፋሽኑ ያለፈበት፣ እየጠፋ ያለ፣….. የሚሉ አስመሳይ የማህበረሰቡን ራስን የመናቅ በሽታ ሳይጠናወታት በራሷ ማንነቷን አስከበረች። ከዚያ በኋላ አሁን ያለንን ጅምላ የማስመሰል ጠባይ አጢና እና ታዝባ ነው መሰል…..”ሁሉ ነገር አርቴፊሻል!” ብላ ዘፍናልናለች።
… ዘሪቱ አልበሟ ከወጣ በኋላ በራስ መተማመኗ ቀጠለ። ያልተለበጠና በዲፕሎማሲ ጭንብል ያልተከለለ አንዳንድ ንግግሮቿ ውዝግብ መፍጠሩ አልቀረም። አንድ ጊዜ ከፋራናይት ናይት ክለብ ጋር አንድ የሙዚቃ ውል ተዋውላ ነበር። በክለቡ በተዘጋጀ ፓርቲ ላይ የምታቀርበው የለስላሳ ሙዚቃ ብቻ ኮንሰርት የምሽቱ ድባብ በሞቅታ ሲቀልጥ “ሙዚቃውን አፍጥኝው!” የሚል ትህዛዝ አዘል ጥያቄ ከዕድምተኛው መምጣት ጀመረ። ዘሪቱ ኦዴንስ ምን ይለኛል? ብላ ሃሳቧን አልቀየረችም። የተዋዋልኩት ለዳንኪራና ለከበርቻቻ አይደለምና የሚያስጨፍር ዘፈን የምዘፍንበት ውል የለኝም! ብላ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋ በውሉ መሰረት በለስላሳው ሙዚቃ እንዳማረብን ብንቀጥል አይሻልም? አለቻቸው። በጄ አልል ሲሏት “ጃንቡሌን” ክፈቱላቸው ብላ በግልፅ ተናገረች። ይሄም እንደ_ንቀት ተቆጥሮ የከተማው መነጋገሪያ ሆነ። እሷ ግን በወቅቱ በየቦታው የሚዘለልበት ዘፈን ጃንቡሌ ስለነበር የእሷ ዘፈን ወገብ ለመፈተሽ ብቁ ስላልሆነና ተቀምጠው የሚያጣጥሙት በመሆኑ አማራጭ መጠቆሟ ነበር። ግን ነገር ማዞር ልማዳችን ነውና በቦታው ያልነበረ ሁሉ በስማ! ስማ ተንጨረጨረ። አንዴም በአካዳሚ ደረጃ ስለዲግሪና ዲፕሎም በተጠየቀች ጊዜ…..”ቆብ ደፍቶ ፎቶ መስቀሉ ትርጉሙ አይገባኝም!” አለች!! በዚህም መሓይም ተብላ ተሞለጨች። በእርግጥ አንዳንዴ ከምረቃው በኋላ እውቀታቸውን ካምፓስ ጥለው የአውራ ዶሮ ዲግሪ የተባሉና በትምህርታቸው ወገን እና ሀገር ማገልገል ትተው ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በሙስና የተዘፈቁ ሙሰኞች የሉም? የእነዚህ ዲግሪ ታዲያ በፍሬም ተሰቅሎ ከግድግዳ ቢውል ዘሪቱ እንዳለችው ምን ትርጉም ይሰጣል? ደሞ ትርጉሙ ካልገባት አልገባትም ነው! የግል ዕይታዋ ነውና ያመነችበትን እከሌ ሳትል መናገር መብቷ ነው።
ዘሪቱ ከመጀመሪያ አልበሟ በኋላ ትደጋግመናለች ብለን ብንጠብቅም እሷ ግን ድራሿ ጠፋ። አንዴ ሙዚቃ አቆመች፣ ሌላ ጊዜ መንፈሳዊ ሆናለች እየተባለ ከመድረክም ራቀች፣ ግን እሷ በሚያልፈው ዕድሜ የሴትነት ወጓ ሰው ብቻ እያዝናናች መጭ እንዲልባት አልፈለገችም። ሙዚቃ የት ይሄዳል? ነገም ይደረስበታልና አሁን ምርጥ እናት መሆን አለብኝ ብላ ከጎጆዋ መሸገች። አራርቆ መውለድ ለሚለው አጉል ስልጣኔና ለምዕራባዊያን ፖሊሲ ሳትንበረከክ በእኩያ ዕድሜ ላይ ያሉ ሶስት ልጆች ወልዳ፣ እንደጥንቱ የእናቶቻችን ዘመን በእናት ጠረን አሳደገቻቸው። እንደዘመኑ ወጣት እናቶች ልጆቿን ለሞግዚት ሳታስነካ…. ውበቴ ይጨማደዳል፣ ሼፔ ከይዞታው ይዛነፋል ሳትል እንደቀድሞ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ሶስቱንም ልጆቿ ጠዋት ማታ ጡት አጥብታና በእቅፏ አሙቃ በትክክለኛ የእናትነት ፍቅር አቆመቻቸው። ልጆቿ ብቻ ሳይሆን ጓደኞቿ ጭምር ስለሆኑት ሶስት ልጆቿ ይሄ ፎቶ ከጽሁፉ በላይ ብዙ ይናገራል። የማይቀረውን የእናትነት ዕዳን ከፍላ ስትመለስ ሙዚቃው የትም አልሄደም ነበርና አግኝታው ተቀላቀለች። በህይወታችን ለሚቀድሙ ወሳኝ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተን በሰዓቱ ስናከናውነው ከዚህ በላይ ስኬት ምን አለ? ከሙዚቃዋ በላይ ለእናትነቷና ለልጆቿ ለከፈለችው እውነተኛ እናታዊ ስብዕናዋ ትልቅ ክብር አለኝ።
“እግዚአብሔር ለፍሬ ያብቃልሽ የውድ ኢትዮጵያዊ ስም ባለቤቷ……….ዘሪቱ ከበደ!!”
The post Artiste Zeritu Kebede, a high self-esteem personality and true Mother: Temesgen Badiso appeared first on Bawza NewsPaper.