..የአሲድ ጥቃት ዓለምአቀፍ የሴቶች አበሳ ነው። ኢትዮጵያም ይሄን ጥቃት ከካሚላት በመጀመር ክፋተኛዋን ዓለም የተቀላቀለች ሲሆን፣ በቅርቡ ከሀገር አልፎ በአሜሪካም ሀገር በሚኖር ኢትዮጵያዊ ይሄው የአሲድ ጥቃት ተፈፅሞ ለማየት በቅተናል። አንድ ክፉ ነገር ለመስፋፋት ማየትና መስማቱ በቂ ነው። የሰዎች ጭንቅላት መጥፎና መልካም ነገሮችን ከየትም አያመጣውም፣ ከሚኖርበት ማህበረሰብ በቀላሉ ይቀርብለታል። በሕንድ በሴት ልጅ ላይ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት ለጆሮ ቅፍፍ ይላል! ይሄን የአስገድዶ መደፈር፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ በባህል ስር የሰደደ ማህበረሰባዊ ተፅህኖ እና ሌሎችም የዘመናት በደሎችን ከሕንድ ሴቶች ጫንቃ ለማውረድና ለመከላከል ተብሎ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችና የወጡ ህጎች በሙሉ እስካሁን ተጨባጭ የሆነ ለውጥ አላመጡም ማለት ይቻላል። በእነዚህ በመሰሉና በፆታቸው ምክንያት የጥቃት ማራገፊያ ወደብ በመሆን የሚታወቁት የሕንድ ሴቶች አሲድም እንደሜክሃፕ የለመዱት ፈተናቸው ሆኖ ኖሯል። ህንድ በሴት ላይ በሚደፋ አሲድም ከዓለም ሻምፒዮን ሆና ዛሬም ቀጥላለች። በተለያዩ ምክንያቶች ወንዶች በሴት ልጅ ላይ አሲድ የመድፋት ክፉ አመል በተፀናወታቸው ሕንድ ውስጥ የችግሩ አሳሳቢነት በማየሉ…….”አሲድ ሰርቫይቨርስ ኤንድ ውመን ዌልፈር” የሚባል የአሲድ ተጠቂ ሴቶች የሚሰባሰቡበትና የሚረዱበት ቋሚ ፋውንዴሽን እስከማቋቋም ህንድን አድርሷታል። እነዚህ የህንድ ሴቶችን ከአሲዱ በላይ የሚጎዳቸው ዋናው ጎዳት በማህበረሰቡ ተቀባይነት ማጣታቸው፣ ወጥተው መማርና መስራት ያለመቻላቸው፣ ከፍቅር ግንኙነት አንስቶ በደረሱበት ሁሉ ሰው እንደአውሬ ስለሚሸሻቸው እነሱም ይሄን በመፍራት ከማዕበራዊ ህይወት ውጪ ሆነው በየቤቱ ራሳቸውን ደብቀው ይኖራሉ። ከቀናቶች በፊት ታዲያ ፋውንዴሽኑ ይሄን መገለልና ሴቶቹ ላይም በራስ መተማመን ለመፍጠር በሞሙቤይ ከተማ በሚገኝ አንድ አዳራሽ ውስጥ በአሲድ የተጠቁ ህንዳዊያን ሴቶችን ያሳተፈ የፋሽን ሾው ትርዒት አዘጋጅቶ ነበር። ይሄ ጥሪ ከተደረገላቸው ሕንዳውያኑ የአሲድ ተጠቂ ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ደፍረው ለመውጣትና ጥሪውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ከአዳራሹ የተገኙት 11 ብቻ ነበሩ። እነዚህ ሴቶች በአሲድ የተጎዳው ፊታቸውን የሚያቆነጁ የሜክሃፕ ባለሙያ ተቀጥሮላቸው፣ ሌሎች ሞዴሎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ከራሳቸው ጋር የሚስማሙ አሪፍ አሪፍ ልብስ በመልበስ በአዳራሹ ለሚገኘው ተመልካች ትርዒቱን በማቅረብ የደስታ ጊዜ አሳልፈዋል።
ከእነዚህ የአሲድ ተጠቂ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው ላዚም አጉዋን እንዳለችው……” ይሄ የአሲድ ጥቃት የደረሰብኝ ዕድሜዬ 15 አመት ሳለ ነው፣ በወቅቱ ለዚህ ጉዳት የዳረገኝ ዕድሜው 34 አመት የሆነው ሰው ካላገባሁሽ ሲለኝ ትምህርቴን መማር እፈልጋለው ስላልኩት አሲድ አምጥቶ ደፋብኝ!” ብላለች። በአዳራሹ ከተጠበቀው በላይ ትኩረት በማግኘታቸውና ደማቅ ዝግጅት መሆኑን የተመለከቱ ሌሎች ተጠቂዎችም በቀጣይ ተመሳሳይ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ መነቃቃትን ፈጥሮላቸዋል የተባለ ሲሆን፣ ይሄው በአሲድ የተጎዱ ሴቶች ፋሽን ሾው በዓለም የመጀመሪያው ተብሎ ተመዝግቧል።
Source: Temesgen Badiso Facebook page
The post Acid attack survivors take part in a fashion show in India appeared first on Bawza NewsPaper.