“ልዤ ዛሬም አልቀናህም?!” እማማ ሥራየ የሃያ ስምንት ዓመት እድሜ ልጃቸው ደርሶ ታፈረ የአንገት ሰላምታ ሰጥቷቸው መደብ ላይ እጥፍጥፍ ብሎ ሲቀመጥ በሀዘኔታ እያስተዋሉት በጉጉት ጠየቁት::
ጥያቄው ከመደጋገሙ የተነሳ ስልችትችት ብሎታል:: የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትኖ ወደ መሰናዶ የሚያስገባ ውጤት ባለማምጣቱ ሥራ ፍለጋ ድፍን የባህር ዳር መሥሪያ ቤቶችን ሲያስስ፣ በየማስታወቂያ ሰሌዳው ዓይኑ እስኪቀላ ሲያፈጥ መዋል ከጀመረ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል::
በየሰው ቤት ልብስ አጥበው፣ ደረቆት ቆልተው፣ እንጀራ ጋግረው፣ አረቂና ጠላ … ያለአባት ያሳደጉትና ያስተማሩት ልጃቸው “ሥራ ይዞ ያልፍለታል፤ እኔንም ያሳልፍልኛል” ብለው ሲያስቡ ከትምህርቱም ሆነ ከሥራው ሳይሆን በመቅረቱ ክፉኛ የሚያዝኑት እማማ ሥራየ ጠዋት ከቤት ወጥቶ ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ውሎ ማታ በገባ ቁጥር ይሄን ጥያቄ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተስፋ ሲያነሱበት ኖረዋል:: አንድም ቀን ግን የተመኙትን ምላሽ አግኝተው አያውቁም:: ሁሌም ድካም፣መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ በተጫጫነው ድምጽ፣ “ኧረ ከንቱ ድካም ነው እናቴ!” ሲል ይመልስላቸዋል:: የዛሬው መልሱም ከዚህ የተለየ አልነበረም:: በፌስታል ጠቅልሎ ይዞት ሲዞር የዋለውን የትምህርት ማስረጃ ሲቀመጡባት እሪታ ከምታበዛው እርጅና ከተጫጫናት ደረቅ ወንበር ላይ እየወረወረ፣ “ኧረ ከንቱ ድካም ነው እናቴ!” በማለት መለሰላቸው::
“አይዞህ ልዤ! ሳለመድኃኒያለም ምኑ ይሳነዋል! አንድ ቀን ይሳካ ይሆናል! አይዞህ!…እኔ እናትህ ደህና ልሁንልህ!” አሉና ከመቀመጫቸው ተነስተው የሚቀማመስ ነገር ሊሰጡት ያረጀ ያፈጀ መሶባቸውን ከፈቱት::
ደርሶ ቀኑን ሙሉ ሲንከራተት በመዋሉ ክፉኛ ስለደከመው የቀረበለትን እንጀራ መብላት ተሳነው:: የጐረሰውን በግራ ቀኝ ጉንጮቹ እያዟዟረ እያላመጠ ባንዳች የሀዘን ስሜት ተውጦ ኑሮ በሚሉት ጠንካራ መዳፍ ታሽተው ታሽተው ከሰውነት ተራ የወጡትን እናቱን እያየ፣ ‘በእሳት እየተቃጠልሽ፣ የማንንም የቸከ ልብስ እየፈገፈግሽ መጠጥ ሽጠሽ አንድ ቀን ሳይደላሽ በዚች የወፍ ጎጆ በምታክል የቀበሌ ቤት ተሸጉጠሽ አስተማርሽኝ:: ከዚህ ሁሉ ድካምና እንግልት በኋላም ደርሸልሽ ልጦርሽ ሲገባ የተገላቢጦሽ አንቺ እኔን ትጦሪኛለሽ:: ይህም ሆኖ አንድም ቀን ፊትሽ ጠቁሮ፣ ተኮሳትሮ ወይም ዞሮብኝ አያውቅም፤ እንደ ጨቅላነቴ፣ እንደ ህፃንነቴ ትንከባከቢኛለሽ፤ ትሳሽልኛለሽ፤ ግን እስከ መቼ?…” እያለ በሀሳብ ሲባዝን እህሉ አልበላህ እንዳለው ያስተዋሉት እማማ ሥራየ የእናትነት አንጀታቸው አላስችልሽ አላቸውና አጠገቡ ቁጭ ብለው እንደ ህፃን እያባበሉ ያጐርሱት ጀመር::
ሊወድቅ ካዘመመው በር አጠገብ መደብ ላይ ተቀምጠው አረቄ በመጠጣት ላይ የነበሩት አባ ቢያዝን በእማማ ሥራየ ሁኔታ ተገርመው፣ “ሥራ ለምን አንቀልባ አምጥተሽ አታዝይውም?!… ሆ!…ሆ!…” ሲሉ አፌዙባቸው::
በሽማግሌው ንግግር የበሸቁት እማማ ሥራየ፣ “አረቄዎን ጠበቅ! አንድ ልጄን ለቀቅ!” አሉና እንጀራ አቅርበውበት የነበረውን ሳህን ሊያስቀምጡ ከመቀመጫቸው ተነሱ::
እማማ ሥራየ ሳህኑን አስቀምጠው ተመልሰው እየተቀመጡ፣ “አንቱየ ይልቁንስ ምናለ ነገሩን ትተው እዚያ እስዎ ተሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ዘበኝነት እንኳን ቢያስቀጥሩት… እስተ አስር ተምሯል… ውትድ ርናም አገልግሏል…” በማለት ለብዙ ጊዜያት ሲያስቡት የነበረውን ጥያቄ አነሱላቸው::
“እኔ ተምሠራበት እንኳን ክፍት ቦታ የለም:: ሥራ የማይንቅ ፣ በመጠጥ … የማይታለል ተሆነ ተጐን ያለው ጋራዥ ባለቤት ዘበኛው በህመም ምክንያት ስለለቀቀበት ምትክ ሳይፈልግ አይቀርም፤ እጠይቅለታለሁ” አባ ቢያዝን ዓይናቸውን ወደ ደርሶ እየወረወሩ መለሱላቸው:: ደርሶ በደስታ ተውጦ በረዥም ከሲታ ሰውነቱ እንደ ሸንበቆ እየተወዛወዘ ሄዶ የአባ ቢያዝንን ጉልበት ሳመ::
አባ ቢያዝን “ተባረክ ልጄ!” ብለው ቀና ሲያደርጉት ከፊት ለፊታቸው እንደቆመ፣ “ኧረ አባባ እኔ ሥራ አልንቅም፣ የተገኘውን ሥራ አክብሬ በትጋት ሠርቼ መለወጥ ነው የምፈልግ…” ሲል ፈጠን ብሎ መለሰላቸው:: ከዚያም እየተወዛወዘ ሄዶ ተቀመጠ::
“አደራ አባቴዋ ቸል አይበሉ! አደራ! ዛሬ ሰው በሰው ተንጠልጥሎ ነው ያለፈለት! አደራ ይሄ የሙት ልዥ የነፍስ ይሆንዎታል!…” አሉ እማማ ሥራየ ልጃቸውንና አባ ቢያዝንን እያያፈራረቁ እያዩ::
“ሥራ ስሚ እንጂ! ያብሮ አደጌ ፣ የልብ ወዳጄ የታፈረ ልዥ እኮ ነው! የዚያ ደግ! የዚያ ሩህሩህ ልዥ!… ቸል አልልም:: እንዳልሁሽ እኔ ተምሠራበት ጋራዥ ቤት በቀኝ ገጣ ያለው ጋራዥ ባለቤት ‘ታማኝ፣ ንቁ… ዘበኛ ፈልግልኝ’ ብሎኛል:: ሰውየው ሲበዛ ደግና ለጋስ ነው:: ከእሱ ተቀጥረው የሠሩት ሲያወሩ እንደሰማሁት በየቀኑ የሚሰጠው ጉርሻ ከደመወዝ ይበልጣል:: እኔ አሁን ታለሁበት ድርጅት ወጥቼ እዚያ መግባቱ ነውር ሆኖብኝ ነው እንጂ…” አሉና ሀሳባቸውን አንጠልጥለው ተውት::
“ቦታው ሁሉ ውስጥ ለውስጥ እየተያዘ የሚያስጠጋኝ አጥቼ ነው እንጅ የሚቀጥረኝ ካገኘሁ ራሴን ጠብቄ በንቃትና በታማኝነት እሠራለሁ” ደርሶ በትዝብት ዓይን እየተመለከታቸው መለሰላቸው::
“ለመሆኑ የት የት መሥሪያ ቤት ጠይቀሀል?” አባ ቢያዝን አረቄያቸውን ተጐንጭተው እያጣጣሙ ጠየቁት::
“አይ አባባ! ‘ምን ያላልንበት ዳገት የለም’ ነው ያለች ኣህያ! ምን ያልረገጥሁት የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅት አለ! ሁሉንም በማስታወቂያ ክፍት የሥራ መደብ ያወጡትን ተቋማት አዳርሻቸዋለሁ:: አንዳንዶቹ አለቆች የትምህርት ማስረጃየን ተቀብለው ሲያስተውሉ፣ ሲመረምሩ፣ሲያጣሩ… ይቆዩና፣ ‘የምንፈልገው ምሩቅና የሥራ ልምድ ያለው ተቀጣሪ ነው:: አንተ ደግሞ ከአስረኛ ክፍል ላይ ነው ያቋረጥህ፤ ላንተ የሚሆን ክፍት የሥራ መደብ የለንም’ ብለው እንደቆምሁ ያሰናብቱኛል:: አንዳንዶቹ ገና በሩን አንኳኩቼ ከፍቼ ስገባ እንቆቆ እንደጋቷቸው ፊታቸውን ኮስኩሰው ባስፈሪ ድምፃቸው፣ “ምን ነበር?!” ሲሉ ይጠይቁኛል::
“ክፍት የሥራ መደብ ማስታወቂያ አውጥታችሁ…” ተናግሬ ሳልጨርስ፣ ለጊዜው ቅጥሩን ሠርዘነዋል፤ በድጋሚ ሌላ ጊዜ ማስታወቂያ እናወጣለን” ይሉኛል:: በሌላ ቀን ተመልሼ ሄጀ ሳጣራ ቦታው ሰው ተቀጥሮበት አገኛለሁ:: አንዳንዶቹ ደግሞ ቢሮ ውስጥ እያሉ ፀሐፊያቸውን፣ “የለም በይ!” ብለው ከበር ሳላልፍ ይመልሱኛል:: አንዳንድ ሰዎችን ሳማክርም ከት ብለው ስቀው፣ “በከንቱ አትድከም፣ የመንግሥትን ደንብና መመሪያ የሚሸራርፈው በበዛበት በዚህ ዘመን ተወዳድሮ በብቃትና በትምህርት ዝግጅት ከመቀጠር ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል” በማለት አንገቴን ያስደፉኛል::
እኔም ተስፋ ቆርጨ ሁሉንም ጣጥየ ወደ ቤቴ ልመለስ አስብና፣ “… የሌለው ልብ የለው” እንዲሉ ተመልሸ በባህር ዳር የአስፋልት ጎዳናዎች እየተመላለስሁ በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ማፍጠጤን እቀጥላለሁ” አላቸው::
አባ ቢያዝን ረዥም ሞጋጋ ፊታቸውን ይበልጥ ያስረዘመውን ረዥም ገብስማ ሪዛቸውን ደጋግመው እየሳቡ፣ በሞጨሞጩ ዓይኖቻቸው እያስተዋሉት ሲያዳምጡት ቆይተው፣ “መንግሥት ያላየው ስንት ችግር በየቦታው ሞልቷል መሰለህ! ቢሆንም እግዜር ላንተ ያለውን እንጀራ አታጣውም፤ ተስፋ አትቁረጥ አይዞህ!” ብለውት ከቤት ወጡ:: እማማ ሥራየም በር ድረስ ሸኝተዋቸው ደጋግመው፣ “ይንሱ አደራ አባቴ! ቸል እንዳይሉ!” ብለዋቸው ወደ ቤት ገቡ::
* * *
ከምሽቱ አራት ሰዓት ሆኗል:: ድንገት የጋራዡ የግቢ በር ተደጋግሞ ተንኳኳ:: ደርሶ ከተጋደመበት የዘብ መጠበቂያ ቆጥ አልጋው በሚደንቅ ፍጥነት ተስፈንጥሮ እየተነሳ፣ “ማነው?!…” ሲል ጠየቀ::
“ክፈተው ደርሶ!… ጠብቀው ነኝ!…” አሉት የጋራዡ ባለቤት፤ ሮጦ ከፈተላቸውና እጅ ነስቶ በሩን ለቀቀላቸው::
ደርሶ በአባ ቢያዝን አማላጅነት በአምስት መቶ ብር ደመወዝ ከአቶ ጠብቀው ጋራዥ ዘበኝነት ከተቀጠረ አንድ ወር እንኳን አልሞላውም:: ከተቀጠረ ጀምሮ አቶ ጠብቀው በዚህ ሰዓት መጥተውበት አያውቁም:: ቀን አልያም እጅግ መሸ ቢባል ማታ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ይመጡና በሚያስፈራ ግርማ ሞገሳቸው ግቢው ውስጥ እየተንጐራደዱ፣ “ደርሶ አደራ ነቅተህ ጠብቅ! ሌባው ተስፋፍቷል” ብለውት ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ:: ወደ ጋራዡ ሳይመጡ የሚውሉባቸው ቀናትም አሉ:: ዛሬ ግና ባልተለመደ ሰዓት መጡበት::
“ምን ፈልገው ይሆን ያለወትሯቸው ከመሸ የመጡ?…” ይህን ሲያሰላስል አቶ ጠብቀው ሁሌም እየተንሸራተተ ትከሻቸው ላይ የማይረጋላቸውን ጋቢያቸውን አስሬ እያጣፉ ትከሻዎቻቸው ላይ እያሳረፉ፣ “አየህ ደርሶ ጊዜው ከተጐዳ በኋላ የመጣሁት ምን ያህል ነቅተህ እንደምትጠብቅ ለማየት ነው:: እውነትም ንቁና ቀልጣፋ፣ ሥራህን አክባሪ ነህ:: እንደዚህ ከሆንህ እኔ አባትህ ተሰው እንጂ ተገንዘብ ብዙም ፍቅር የለኝም፤ እጄ አይሰስትም:: ተትልቅ ደረጃ ነው የማደርስህ!” ብለው አንድ መቶ ብር የያዘ እጃቸውን ዘረጉለት::
“አባባ የደመወዝ ቀን እኮ ገና አልደረሰም! አራት ቀን ይቀረዋል!” አላቸው በተገርሞ አንዴ ብሩን፣ አንዴ ትልልቅ ዓይኖቻቸውን እያየ::
“ደመወዝ አይደለም! ደመወዝ ቢሆንስ በመቶ ብር ነው እንዴ የተቀጠርህ?! ተቀበል!” አሉት ቀና ብለው እያዩት::
ደርሶ ግን፣ “አሻፈረኝ!” አለ:: ጨዋነቱ፣ ይሉኝታው፣ ትህትናው ይበልጥ እንዲወዱት እያደረጋቸው ብሩን በሸሚዝ ኪሱ ሸጉጠውለት ወጡ::
ደርሶ አንድ መቶ ብሩን አስሬ ከኪሱ እያወጣና መልሶ እየከተተ፣ ደግሞም አገላብጦ እያየ እንደ በኩር ልጅ ሲስመው ብዙ ቆየ:: “አቶ ጠብቀው እውነትም ሲበዛ ለጋስና ደግ ሰው ናቸው” እያለ ሲያመሰግናቸው፣ ዕድሜና ጤና፣ ሀብትና ብልጽግና… ሲመኝላቸውም አመሸ:: በመጨረሻም ያንኑ መቶ ብር ለምን ለምን ጉዳይ ሊያውለው እንደሚችል ሲያሰላስል እንቅልፍ ሸለብ አደረገው::
አቶ ጠብቀው ሶስትም አራትም ቀናት እያሰለሱ ከመሸ በኋላ እየመጡ ሀምሳ፣መቶ፣ ሁለት መቶ ብር በብዙ ልመና ለደርሶ መስጠታቸውን ቀጠሉ:: መጀመሪያ አካባቢ “አልቀበልም!” እያለ አስቸግሯቸው ነበር:: ቀን አልፎ ቀን በተተካ ቁጥር ግን ለይስሙላ፣ “ኧረ አባባ አይገባም!” በማለት ትንሽ ከተግደረደረ በኋላ የዘረጉለትን ገንዘብ ፈጥኖ ይቀበላቸው ጀመር:: ቀስ በቀስም የአጉል ልማድ እስረኛ ሆነና አምሽተው በመጡ ቁጥር እስኪታዘቡት ድረስ እንደ ውሻ እጅ እጃቸውን ማየት ጀመረ:: እሳቸውም ያስለመዱትን ገንዘብ ሸጐጥ ማድረጋቸውን አላቋረጡም::
ደርሶ አሠሪው አቶ ጠብቀው የሚሰጡትን ጉርሻ መጀመሪያ አካባቢ ሳይቀንስለት ለእናቱ በመስጠት ኑሯቸውን ይደጉም ነበር:: ስለሚሰጠው ገንዘብ መጠንና ለምን እንደሚያውለው፣ ስለአቶ ጠብቀው ደግነት ግራና ቀኝ የሚገኙትን ጋራዦች ለሚጠብቁት ዘበኞች ያወራላቸው ጀመር:: ዘበኞቹ ደርሶ ከእነሱ በኋላ ተቀጥሮ የእነሱ አሠሪዎች የማይሰጧቸውን የገንዘብ ጉርሻ በማግኘቱ፣ ገንዘቡን ከማግኘቱም በላይ ለእናቱ መስጠቱ ቅር እያሰኛቸው መጣ:: ሰይጣናዊ ቅናትም አደረባቸው::
አውጥተው አውርደውም አንድ ነገር ወሰኑ:: ወሰኑናም ሊተገብሩት ቆርጠው ተነሱ:: አቶ ጠብቀው ደርሰው የተመለሱባትን ምሽት በጉጉት እየጠበቁ፣ “አንተስ ምንም የማይደማህ ነህ! ባይሆን እኛ እንጋብዝህ!” እያሉ በብዙ ውትወታ በአካባቢው ወዳሉ መጠጥ ቤቶች እየያዙት ይወጡ፣ ይጠጡ፣ ያጠጡት ጀመር:: ለጥቂት ቀናት እነሱ ሲጋብዙት ይሉኝታ ቢጤ ተሰማውና እሱም እነሱን መጋበዝ ለመደ::
በእነሱ ገፋፊነት እንዲህ እንደ ቀልድ የተጀመረው መጠጥ ቀስ በቀስ እስረኛው አድርጎት ሊወጣው በማይችለው አዘቅት ዘፈቀው:: በመጠጥ ሱስ በጣም ከመጠመዱ የተነሳ አቶ ጠብቀው ቶሎ መጥተው ያስለመዱትን ሸጉጠውለት እስኪሄዱም ይቸኩል ጀመር::
* * *
አቶ ጠብቀው ወደ ጋራዣቸው መጥተው ለደርሶ ሁለት መቶ ብር ሸጉጠውለት ከሄዱ ሁለት ሰዓት ሆኗቸዋል:: ሶስቱ ጓደኞቹና እሱ በቅርብ ርቀት ካሉት መጠጥ ቤቶች የተሰየሙት አቶ ጠብቀው እግራቸው ከጋራዥ ገና ወጣ ከማለቱ ነበር:: ይሁን እንጂ፣ ሁለቱ ጓደኞቹ “በቃን! ከዚህ በላይ አንጠጣም! እናንተ ተጫወቱ” ብለው አንድ ጓደኛቸውንና ደርሶን ትተዋቸው የወጡት ከአንድ ሰዓት በፊት ነበር::
ደርሶና ጓደኛው ቢራቸውን ሲያንደቀድቁ ድንገት ጋራዦቹ ከሚገኙበት አካባቢ ጫጫታ፣ ከዚያም ተደጋግሞ የጥይት ድምፅ ተሰማ:: ደርሶ እጅጉን ደንግጦ መጠጡን በአንድ ትንፋሽ ጨልጦ ተነሳ::
ጓደኛው ምንም እንዳልተፈጠረ፣ “ቀስ በል እንጂ! ምነው?… ተረጋጋ!…. “ አለው::
ደርሶም፣ “ከአህያ ጋር የዋለች ላም ምን ተምራ ትመጣለች!” አሉ:: እናንተን ተከትየ መጠጥ ቤት ተወዝፌ እያመሸሁ ጉድ ሳልሆን አልቀረሁም! ወይኔ! ደርሶ! እናቴ ‘ሠርቶ ያሳልፍልኛል! እሱም ያልፍለታል! ‘ስትል!…” አለና ገላምጦት ወደ ጋራዡ ሮጠ::
ጋራዡ ደርሶ በሩን አልፎ ሊገባ ሲል፣ “ባለህበት ቁም! ልክስክስ ሰካራም!…” የሚል ነጐድጓዳማ ድምፅ ቀልቡን ገፈፈው:: ግቢው ጨለምለም በማለቱ ሰዎቹን በርቀት ለመለየት ባይችልም ድምፁ የአቶ ጠብቀው መሆኑን በቅጽበት ተረዳ:: ባለበት ደርቆ እንደቆመ ወደ ግቢው ተመለከተ:: ሰዎቹ ወደ እሱ እየመጡ መሆኑን አስተዋለ:: ወደ እሱ ሲጠጉ ዓይኑን ማመን አልቻለም:: አቶ ጠብቀውና ሶስት ፖሊሶች አብረውት ሲጠጡ ቆይተው ቀድመው የወጡትን ሁለቱን ዘበኞች፣ “ሌባ! ሞላጫ! መንታፊ! እሱን በመጠጥ ሱስ አስራችሁ፣ተብትባችሁ! እናንተ ልትሠርቁ መጣችሁ! “ እያሉ የሠረቁትን የመኪና መለዋወጫ ዕቃ እንደያዙ እያዳፉ ከጋራዡ ግቢ ሲያስወጧቸው ተመለከተ:: በሩ ጋ እንደደረሱ ፖሊሶቹ እሱንም እየገፉ ፣ “ሂድ ተቀላቀል! አንተም እስረኛ ነህ! “ሲሉት በሀፍረትና በድንጋጤ አንገቱን እንደደፋ በፖሊሶች እየተገፋ ከጓደኞቹ ጋር ተቀላቀለ::
ምንጭ፡- በኩር
The post እስረኛው – አጭር ልቦለድ appeared first on Bawza NewsPaper.











