አንዳንዱ የፌስቡክ አክቲቪስት : ዳግም አረቄ እንደጠጣ አብሿም የቆሎ ተማሪ የዞረበት ነው::
ለምሳሌ አንዱ ምላሱን አድጦት ይሁን አስቦበት አንድ ዘረኛ ነገር ይፅፋል ወይም ይናገራል:: ዘረኛውን ፅሁፍና ንግግር አይተህ እንዳላየህ ካለፍከው የትም አይደርስም:: በራሱ ጊዜ ይከስማል:: ዘረኝነትን መዋጋት የሚቻለው ዘረኞች የሚስገበገቡለትን ትኩረት በመንፈግ ነው:: ግን የወሬ ሀራራ የሚያስፏሽከው ስፍር ቁጥር የለሽ አክቲቪስት ባለበት ሀገር ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም::
“በዘር አላምንም ” የሚለው አክቲቪስት: ከሰው ጏሮ ዘሎ ገብቶ: ዘረኛ ፅሁፍ ጎርጉሮ አውጥቶ: ሼር ያደርግና ውግዘቱን ያዥጎደጉደዋል:: ቀጥሎም : እጅ እጅ የሚል የሚል ገለባ ምክር ያስከትላል:: ወይም በናት አገሩ ላይ ያሟርትና “ኧረ ወዴት እየሄድን ነው? ” በሚል የዛገ ጥያቄ ይጠምደናል:: ክፉ ሀሳብን በማራባት ክፋትን ለማስወገድ መሞከር አይቻልም::
ባገራችን የሆነ ቦታ ግጭቶች ይነሳሉ:: ከዚያ ያካባቢ ሽማግሌዎች ጉዳዩን በሽምግልናና በእርቅ እያረጋጉት ነው የሚል ዜና ይወጣል:: የግጭቱን ዜና እያጋጋለ የሚነዛ የመበርከቱን ያህል : የእርቁን ዜና ከመጤፍ የሚቆጥረው የለም:: በጦርነት የኖርን ህዝቦች ስለሆን ገና የጦርነት አዚም( ሀንጎቭር ) አለቀቀንም:: ስለ እርቅ ስለ ሰላም በስፋት መተንተን የሚያስችለን በቂ የቃል ክምችት የለንም::
ደሞ ያክቲቪስት ነኝ ባዩ ትንታኔ ሁላ የሚጠናቀቀው ሌላውን በመወንጀል ነው:: ሁሉም ሌላውን ለመውቀስ ከመሞከሩ በፊት የችግሩ አካል መሆኑን የሚገነዘበው መች ነው??
በምርጫ ዘጠና ሰባት መባቻ ማግስት ተከሰተ የተባለ ነገር ትዝ ይለኛል:: በመንግስት ሸፍጥና ግፍ የተቆጡ ወጣቶች የረከቦት ጎዳናን በድንጋይ አጥረው: ጥሶ ለማለፍ የሚሞክር አውቶብስ ሲያዩ በድንጋይ ይወግሩት ነበር::
ትንሽ ቆይቶ አንድ ሰገራ ጭኖ የሚያልፍ የፍሳሽ አስወጋጅ ቦቲ መኪና ብቅ አለ:: የመንደሩ ጎረምሶች ከበቡና ድንጋይ አዘነቡበት:: ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ በድንጋይ ወንፊት ከሆነው ጋቢና ውስጥ አንድ የተጎሳቆለ ሽማግሌ ሹፌር ዱብ አለ:: ባንድ እጁ የተፈነከተ ግንባሩን ሸፍኖ በሌላ እጁ ወደ ከበቡትን ጎረምሶች እየጠቆመ እንዲህ አለ::
” እንያንዳንድሽ ይህን ቦቲ የሞላው የመለስ ዜናዊ አር ብቻ ከመሰለሽ ተሳስተሻል !! ብታምኚም ባታምኚም እያንዳንድሽ አዋጥተሻል!
“Bewketu Seyoum በእውቀቱ ሥዩም
The post Ethiopia: Facebook Activist! appeared first on Bawza NewsPaper.