ሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዲፕሎማሲ እና ወታደራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ ሀገራዊ ክብርና ልዕልናዋን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና እንዳለው ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡ ብሄራዊ ፍላጎትና ጥቅም በሌላ ቋንቋ የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ማለት በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት ከህገ-መንግስቱ የሚመነጩ ግልጽ ተልዕኮዎችን አንግቦ ለህዝብ ፍላጎት የሚገዛና ለህዝብ ጥቅም የሚሰራ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የተለያዩ ሀገሮች የመንግሰት ምስረታ ታሪክ እንደሚያሳየው በ19ነኛውና 20ኛው ክ/ዘመን በፊት የሀገር ጥቅምና ፍላጎት የሚመነጨው ከተለያዩ የገዥ መደቦችና እምነት ተቋማት እንደሆነ የጠቆሙት ጠ/ሚሩ ዘመናዊው ብሄራዊ ጥቅምና ፍላጎት አረዳድ ግን ህዝብና ህዝብን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የብሄራዊ አቅም ዋነኛ መገለጫ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ግቦች ማሳካት እና የሀገሪቱ ህዝቦች ክብርና የሀገር ሉዓላዊነት ማስከበር ናቸው ብለዋል፡፡
ዘመናዊው ጦርነት ከመደበኛ የጦርነት አውድ የተለየ ቅርጽና መልክ አለው፡፡ መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ የጦርነት ተዋናዮች የሚሳተፉበት፣ የግለሰቦች እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን የማድረግ አቅም ያመጠቀ የቴክኖሎጂ እድገት መኖር እና አለማ-ቀፋዊነት ያመጣው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የባህል ትስስር ከፍተኛ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የዘመናዊ ጦርነት ምህዳሩን ባህሪያት አስረድተዋል፡፡
የጦርነት ስልቱም አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ከሚደረግ ጥረት ይልቅ የተፃራሪ ኃይሎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶችን የሚያሳትፍ፣ የተፃራሪ ሀይልን ውሳኔ ሰጪ አካላት ስትራተጂ እቅድ እንዳይሳካ ወይም ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ እንዲታይ ማድረግን መሰረት ያደረገ የጦርነት ስልት ነው ብለዋል።
ዘመናዊ መደበኛ ጦርነቶች የሚያስከፍሉት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መግስታት በቀጥታ ጦርነት ከመግባት ይልቅ የውክልና ጦርነትን መምረጥ የሚታይበት ምህዳር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የምንገኝበት የአራተኛው ትውልድ ጦርነት አለም በነገሮች እና በኩነቶች መተሳሰር ምክንያት አንድ አካባቢ የሚከሰት ድርጊት አለማቀፋዊ በሆነ መልኩ ቀውስን የሚያስከትል ነው። በነገሮች እና በኩነቶች መተሳሰር እጅግ በጠነከረበት በዚህ ዘመን የሚያጋጥሙ ስጋቶችን መረባዊ የሆኑ በመሆናቸው ፣ስጋቶቸን መመከት የሚቻለው በመረባዊ አደረጃጀት ነው ብለዋል።
ይህንን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት መከላከያ ሰራዊቱ ራሱን በቀጣይ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ማስገባት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሪፎርሙ መነሻ ሁኔታዎችም የሀገሪቱ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ሁኔታችና በአጠቃላይ የህዝብ ስሜት ነው ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዙሪያ መለስ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ በመቆየት ከፍተኛ አደጋ ያንዣበበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት ጠ/ሚኒስትሩ ችግሩን የፈጠረው መንግስት ችግሩን መፍታት አይቻልም እስከ መባል የደረሰ ትችት ቢደርስም ተግዳሮቱን ወደ እድል በመቀየር ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በአፋጣኝ መውሰድ በመጀመሩ የህዝቡን ተስፋ በድጋሚ በማግኘት ለውጡን ለማስፋትና ለማጥለቅ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የመከላከያ ሀይል በኩል ያለው ዋነኛ ቁልፍ ሪፎርም ጉዳይ የሰራዊቱን ፕሮፌሽናሊዝም ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሲባል የሰራዊቱን ሙያዊ ብቃት፣ ሃላፊነት የመውስድና የተሟላ ሰብዕና የተላበሰ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ሰራዊቱ በመርህ የሚገዛና ለወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተጽዕኖ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከበር ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በቅርቡ በተደረገው የመንግስት ስልጣን ሽግግር ወቅትም ሰራዊቱ ያሳኘውን ሙያዊ ዲሲፕሊን ያደነቁት ጠ/ሚኒስትሩ ይህ ፕሮፌሽናሊዝም መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የመከላከያ ወሳኝ አቅሞች ለማሰደግ በምድር ሀይልና በአየር ሀይል በአፍሪካ ቀደምት ሀገሮች ተርታ ያስቀመጠንን ሀይል ገንብተናል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ የባህር ሀይል አቅምም በቀጣይ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢፌድሪ ህገ -መንግስት መከላከያ ሰራዊቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦች ነጸብራቅ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት መጽዳት፣ ለሲቪል አስተዳደርና ለህገ -መንግስቱ ተገዥ መሆን፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮ ያሰቀመጠ በመሆኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህገ-መንገስታዊ ባህሪው ጠብቆ መዝለቅ አለበት ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ዋነኛ አላማ በሲቪል አስተዳደሩ የሚቀመጡ ሀገራዊ ስጋቶችና የደህንነት ስጋቶችን በተቀመጠለት ትርጓሜ መሰረት በላቀ ብቃት ግዳጁን የማስፈጸም፣ የህዝብን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስከበር እና የሀገር ክብርና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ለበለጠ ቪዲዮውን ይመልከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች የደረጉት ገላፃ
Posted by Bawza Ethiopian Newspaper on Friday, June 1, 2018
The post PM Dr. Abiy Ahmed presentation to Higher military officials appeared first on Bawza NewsPaper.